• News

 • የዶላር የኮንትሮባንድ ዝውውርን ለማሳለጥ የብሄር መልክ ያለው ግጭት ተቀስቅሷል 31 October 2017 | View comments

 • የዶላር የኮንትሮባንድ ዝውውርን ለማሳለጥ የብሄር መልክ ያለው ግጭት ተቀስቅሷል
  · 2 ሚ. ዶላር በህገ ወጥመንገድ ሲዘዋወር ተይዟል
  · የክልሎቹ የመንግስት ሚዲያዎች ግጭቱን ለማቀጣጠል ሞክረዋል
  · ፖሊስ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ መሆን አለበት
     በመቶዎች ለሚቆጠር ህይወት መጥፋትና ለመቶ ሺዎች መፈናቀል ምክንያት የሆነው የኦሮሚያ ሶማሌ ግጭት መንስኤው የድንበር ጉዳይ አይደለም ያሉት ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ የግጭቱ ዋነኛ ምክንያት መንግስት ያልፈታው የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ነው ሲሉ ከትላንት በስቲያ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ገልፀዋል፡፡
  በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ የጫት ንግድ “በሞኖፖል” ለመያዝ የሚደረገው ጥረት ግጭቱ የብሄር መልክ እንዲይዝ አድርጎታል ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ በተደረገ ፍተሻ 2 ሚሊዮን ዶላር በህገ ወጥ መንገድ በመስመሩ ሲዘዋወር በቁጥጥር ስር መዋሉን ጠቁመዋል፡፡ በአካባቢው ያለውን የዶላር የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ለማሳለጥም ሆን ተብሎ የብሄር መልክ ያለው ግጭት እንዲቀሰቀስ ተደርጓል ብለዋል ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
  አቶ ኃይለማርያም “ጥገኛ ኃይሎች” ሲሉ የገለጿቸው አካላት፤ ይሄን ግጭት ያስነሱት በዶላር ህገወጥ ዝውውር መቀጠል እንደማይችሉ በመረዳታቸው፣ ከግርግሩ ለመጠቀም እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
  “ግጭቱ የተፈጠረው በህዝቦች መካከል ቅራኔ ስላለ አይደለም” ፣“የሁለቱ ክልል ህዝቦች ለዘመናት አብረው በፍቅር የኖሩ፣ የሚዋደዱና የሚተሳሰቡ ናቸው” ብለዋል ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
  በግጭቱ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ሰዎች መኖራቸውን በመግለፅም መከላከያ ሠራዊት በፍጥነት ደርሶ ሁኔታውን ባያረጋጋ ኖሮ ከፍተኛ እልቂት ይፈጠር ነበር ያሉት አቶ ኃ/ማርያም፤ ከዚህ አንፃር መከላከያ ሠራዊቱ ፈጥኖ አልደረሰም የተባለው ተቀባይነት የለውም ሲሉ አስተባብለዋል።
  በግጭቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋምም በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ አገር አቀፍ ኮሚቴ ተቋቋሞ ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡  በሁለት ክልሎች ነዋሪ ህዝቦች የጋራ የሠላም ኮንፈረንሶች ለማካሄድ እቅድ መያዙን የገለፁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በሃገር አቀፍ ደረጃም መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያሣትፉ ተመሳሳይ የህዝብ ጉባኤዎች ለማካሄድ መንግስት ሰፊ እቅድ መያዙን ጠቁመዋል፡፡
  የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል የመንግስት ሚዲያዎችም ግጭቱን የበለጠ ለማቀጣጠል መሞከራቸውን የጠቆሙት አቶ ኃይለ ማርያም፤ ህጉ- በሚፈቅደው መሠረት ሚዲያዎች አደብ እንዲገዙ ይደረጋል ብለዋል - የሃገሪቱ ሚዲያዎች ግጭትን ከማባባስ እንዲቆጠቡም በማሳሰብ፡፡
  በግጭቶቹ ላይ የተሳተፉ የልዩ ሃይል ፖሊስ አባላት እንደነበሩ የጠቆሙት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የፖሊስ ሃይሉ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ እስካልተደረገ ድረስ ለአንዱ ወግኖ መዋጋቱ አይቀርም ብለዋል። እንዲያም ሆኖ በግጭቱ ወቅት ህገ መንግስታዊ ኃላፊነታቸውን የተወጡም መኖራቸውን አልሸሸጉም፡፡ “ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሃገሪቱ የፖሊስ ስታንዳርድ ምን መሆን አለበት በሚለው ላይ አቅጣጫ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፤ ከዚህ አንፃር እስከ ዛሬ ጉድለት አለብን” ብለዋል። ባለፈው የክረምት ወራት የሃገሪቱ የፖሊስ ስታንዳርድ ምን መሆን አለበት በሚል ረቂቅ መዘጋጀቱንና ለፓርላማው ቀርቦ ከፀደቀ በኋላ በስራ ላይ እንደሚውልም ገልፀዋል፡፡
  ለግጭቱ መሰረታዊ መፍትሄውም ፖለቲካዊ መሆኑን የተቆሙት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ትግሉ በአካባቢው የሚታየውን ኪራይ ሰብሳቢነት በሚደፍቅ መልክ ካልተካሄደ በስተቀር ለወደፊትም ቢሆን ግጭት ለማስቆም የሚቻል አይሆንም ብለዋል፡፡
  በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል ድንበር ሪፈረንደም በተካሄደባቸው አካባቢዎች ተግባራዊ ማካለሉን ለማከናወን አዳጋች ነገር እንደሌለም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

   
  « Back to archive
 • Leave your comment

 • Name:
   
  Email:
  Comment   
  captcha
  Enter the code shown above: