• News

 • “ አባባ ጃንሆይ ” 29 November 2017 | View comments

 • “ አባባ ጃንሆይ ”

  ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ አንድ መቶ ሀያ አምስተኛ ዓመት የልደት በዓል የተዘጋጀ ማስታወሻ ቴዎድሮስ አበበ

  ከ አንድ መቶ ሃያ አምስት ዓመታት በፊት በሐምሌ ወር፣ በአስራ ስድስተኛው ቀን የተወለዱት ተፈሪ መኰንን ከንግሥና ስማቸው ይልቅ ሕዝባዊ ፍቅር የተላበሰው የቅጽል ስማቸው በእጅጉ ደስ ይለኛል ። ለምንድነው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ይህንን " አባባ ጃንሆይ " የሚለውን ስያሜ የተጐናጸፉት ? ብዙ ምክንያት መደርደር ቢቻልም ለእኔ መልሱ አንድ ይመስለኛል ፤ ታላቁ መሪ የኢትዮጵያ ልጆች በትምህርት እንዲያድጉና እንዲበለጽጉ በጽኑ ፍላጐት፣ በከፍተኛ ትጋትና በአባታዊ ፍቅር ይሠሩ ስለነበረ ነው። አንድ አባት ልጆቹ ተምረው ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲደርሱለት ብዙ ጥረት እንደሚያደርግ ሁሉ አባባ ጃንሆይም ልዩነት ሳያደርጉ ይህንኑ ያከናውኑ እንደነበረ ብዙ፣ እጅግ ብዙ ማስረጃዎችን ማየትም፣ ማሳየትም ይቻላል። በዚህ የአባባ ጃንሆይ ራዕይ ተጠቅመው አገራቸውን ከጠቀሙ ብዙ ሰዎችም የምስክርነት ቃል ማግኘት አይከብድም ።

  ከሁሉም በላይ ግን ትምህርትን በተመለከተ ራሳቸው አባባ ጃንሆይ የተናገሯቸውና በታሪክ ገጾች ላይ የተመዘገቡ አያሌ ንግግሮቻቸው ለመግለጽ ከምችለው በላይ ስሜቴንም፣ ልቤንም ይነኩታል። እኒህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ና የመላው ጥቁር ሕ ዝብ አንጸባራቂ ኰከብ ስለትምህርት የነበራቸውን አመለካከትና አገራዊ ራዕይ እንዲሁም ያከናወኗቸውን ታላላቅ ሥራዎች በዚህ ዘመን ማስታወስ ያስፈልጋል ፣ በእጅጉም ይጠቅማል ። ስለሆነም የግርማዊነታቸው ንግግሮች ከተመዘገቡባቸው የ " ፍሬ ከናፍር " መድብሎች ውስጥ ከላይ ያነሳሁትን ነጥብ የሚያጠናክሩ ዐንቀጾችን በጣም በጥቂቱ መራርጬ ልደታቸውን ለመዘከር ወደድኩ።አባባ ጃንሆይ የንጉሠ ነገሥትነቱን ዙፋን ከመውረሳቸው በፊት ነበር ትምህርትን የማስፋፋት ሥራ በሰፊው የጀመሩት። ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፲፱፻፲፯ ዓ . ም . ( የዛሬ ዘጠና ሁለት ዓመት ) የተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤትን መርቀው ሲከፍቱ የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ ነበሩ። የዚያን ዕለት ያደረጉትን ንግግር እንደሚከተለው ነበር የጀመሩት፤

  የተወሰነ ቦታ የሌለህ፣ በሁሉ የመላህ አምላካችን ሆይ በፈቃድህ ያስዠመርከኝን ያስፈጸም ከኝ፤ ይህንንም እንድናገር የፈቀድክልኝ፤ ምስጋና ላንተ ይሁን። ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንን በዚህ ንግግራቸው ትምህርትና ዕውቀት ለኢትዮጵያ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ፣ በዚህም ረገድ ዳግማዊ ምኒልክ ያከናወኑትን ትልቅ ሥራ ከጠቀሱ በኋላ የሚከተለውን ተናግረው ነበር፤ . . . ለሀገሬ ለኢትዮጵያ ወዳጅ ነኝ የሚል ሰው ሁሉ የወዳጅነቱን ምልክት ለማሳየት ተማሪ ቤት መርዳትና የሚቻለው ተማሪ ቤት መ ሥራት፣ ልጁን ማስተማር የሚገባ ነገር ነው። ይህንንም የሚያደርጉ ሁሉ በውነት የሀገራቸውን ፍቅር ገለጹ ማለት ነው።

  . . . እግዚአብሔርም ቢያድለኝ ይህች ተማሪ ቤት መከፈቷን አይቼ ደስ እንዳለኝ፤ ተምራችሁ ለሀገራችሁ መርዳትን፣ በኢትዮጵያ ትምህርት መስፋቱ ን ና ተማሪ ቤት መብዛቱን እንዲያሳየኝ እመኛለሁ። ንግግራቸውንም የደመደሙበት ቃል እንደሚከተለው ይነበባል፤  አሁንም የልቦናችሁ መሠረት እግዚአብሔር ን በመፍራት፣ አገርን በመውደድ የተጠመደ እንዲሆን እግዚአብሔር የሁላችንንም የልባችንን መሠረት ከዚህ ያድርገው ብዬ ርኅሩኅ ፈቃዱን እለምናለሁ። ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፤ ኢትዮጵያ ሕያውት ትሁን። ይገርማል ! ኢትዮጵያ የእግዚአብሔርን ስም በሙሉ ልብ ደጋግሞ የሚጠራ የአገር መሪ ካየች ሰነበተች። ታኅሣሥ ፳ ቀን ፲፱፻፲፱ ዓ . ም . ( ከዘጠና ዓመታት በፊት )

  ወደ ውጭ አገር ለትምህርት የሚሄዱ ሀያ አንድ ተማሪዎችን ሲሰናበቱ ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንን ከተናገሩት ውስጥ ጥቂት ልጥቀስ፤

  አሁን እንደምትሄዱ እንደናንተም ወደ አውሮፓ መላክ ከጀመርን ፭ እና ፮ ዓመት ሁኑዋ ል ። ከዚህ ቀደም በሄዱት ልጆች ሁሉ ክፉ ስም አልሰማንምና እናንተም አንድነት ኃይል ነው፣ መለያየት ጉዳት ነው የተባለውን ሳትዘነጉ የኢትዮጵያን ስም በማስከበርና በማስመስገን በሚገባ ትሕትና ተግታችሁ ተማሩ፤ እናንተ ግን ክፉ ብትሠሩ እናንተ ብቻ ተሰድባችሁ አትቀሩም ላገር ስድብ ትሆናላችሁ እንጂ። በተማራችሁትም ፍሬ አገራችሁን እንድትረዱ መርጠን ሰደናችኋልና . . . ለማትሞተው ኢትዮጵያ በሰላም ተመልሳችሁ እረዳት እንድትሆኑዋት እግዚአብሔርን እንለምንላችኋለን። ደህና ሰንብቱ።

  ወጣቱ አልጋወራሽ ከንግሥና ዘመናቸው በፊትም ሆነ " ንጉሥ " ተብለው በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት የንጉሥነትን ዘውድ ከጫኑ በኋላ ብዙ ቁምነገሮ ችን አከናውነዋል። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተብለው የንጉሠ ነገሥትነቱን ዙፋን ከወረሱ በኋላ ደግሞ ይህንን ትምህርት የማስፋፋት ተልዕኰ ይበልጥ አጠናክረው ቀጠሉበት። ታኅሣሥ ፱ ቀን ፲፱፻፵ ዓ . ም . ( የዛሬ ስድሳ ዘጠኝ ዓመት ) ወደ ውጭ አገር ለትምህርት ለሚሄዱ ተማሪዎች ከሰጡት የምክር ቃል ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፤

  መማር እጅግ መልካም ነገር ነው። መማር እናንተንም፣ እኛንም፣ አገራችሁንም ይጠቅማ ል። እኛም እናንተም እናልፋለን፤ አገር ግን አያልፍም። የሚተላለፍ ትውልድ እየተራባበት ይኖራል ። ያልተማረ ትውልድ የሚኖርበት አገር በባዕድ እጅ ይወድቃል። ትውልዱም ይረገጣል። የተማረ ትውልድ የሚኖርበት አገር ግን የሚደፍረው የለም። ኢትዮጵያም ከተማረች አትረገጥም። አ ባቶቻችሁ በሥጋ ወለዷችሁ። እኛ ግን አእምሮአችሁን በማጐልመስ ወለድናችሁ። እግዚአብሔር ደግሞ ሁላችንንም በመንፈስ ይወልደናል። አለመማር ሥጋንም ነፍስንም ይጐዳል። የሥጋ ትምህርት ለሥጋ ጥቅም ይረባል። መጐጃውም ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ከሁሉ አብልጦ መንፈሳዊ ትምህርት እግዚአብሔርን መፍራት ለሁላችሁ አስፈላጊ መሆኑን እንዳትዘነጉ አደራ እንላችኋለን።

  በዚያው ዓመተ ምሕረት ኅዳር ፲፫ ቀን በአዲስ አበባ የሚገኘው የናዝሬት ትምሕርት ቤት ሲመረቅ አባባ ጃንሆይ እንዲህ ነበር ያሉት ( ሴቶችንና ትምህርትን በተመለከተ ) ፤

  በዛሬው ጊዜ ሴቶች በወንድ መከታ ሆነው እርሱን ብቻ እያገለገሉ በመኖር ፋንታ በየቦታውና በየጊዜው በልዩ ልዩ ሥራና ትምህርት ገፍተው የወንድ ሥራ በተባለው ሁሉ እየተተኩ፣ በሰላማዊ ሥራ እየገቡ ማገልገል ብቻ ሳይሆን መሣሪያም ይዘው በጦርነት ጊዜ በአደረጉት አገልግሎት ለአገራቸው እርዳታና ክብር የሚሰጡ መሆናቸውን አስመስክረዋል። እናንተም በየጊዜው ስንጐበኛችሁ ፍሬ እንዳታጡ የምንሰጣችሁን ምክር እያ ስታወሳችሁ በትምርታችሁ የገፋችሁና ባለሞያዎች ሆናችሁ እንድትገኙ ምኞታችን ነው። . . . ስለዚህ በዚህ የትምህርት ቤት ለመገኘት የታደላችሁ ሁሉ ለአገራችሁ መልካም ዕድል መሣሪያ እንድትሆኑ፣ በትምህርት እንድትገፉ የዘወትር ምኝታችን ነው።

  ጳጉሜን ፬ ቀን ፲፱፻፵ ዓ . ም . ለት ም ህርት ወደ ውጭ አገር የሚላኩት ተማሪዎች አባባ ጃንሆይ ፊት ቀርበው ሲሰናበቱ ንጉሡ የተማሪዎቹን ተወካይ መልእክት ካዳመጡ በኋላ ከተናገሩት የምክር ቃል ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፤

  ዓለም እንደጋሪ እግር ተዘዋዋሪ ነው። አሁን የምትሔዱበት አገር ልዩ ልዩ ዕውቀትና ጥበብ የሚገኝበት ነው። ነገር ግን ንግግር ዋስ የለውም። የሰው አገልግሎቱ፣ ጠቃሚነቱም የሚታወቀው በሥራው ነው። ለወደፊ ት ለ ኢትዮጵያ እድገት ትጠቅማላችሁ ብለን አደራ ስንጥልባችሁ ለምን ጉዳይ እንደተላካችሁ፣ ስትመለሱም ምን ፍሬ ይዛችሁ እንደምትመጡ አሁን ማሰብ አለባችሁ። ደጋግመን አደራ የምንላችሁ መሔዳችሁን ብቻ ሳትመለከቱ ሔዳችሁ ስትመለሱ የምታመጡት ፍሬ በተስፋ የሚጠበቅ መሆኑን እንዳትረሱ ነው። እግዚአብሔር መንገዳችሁን ያብራላችሁ።

  ኅዳር ፩ ቀን ፲፱፻፵፪ ዓ . ም . የግርማዊት እቴጌ መነን ትምህርት ቤትን ሲጐበኙ ደግሞ ለተማሪዎቹ ከሰጡት መሪ ቃል ውስጥ የ ሚ ከተለው ይገኝበታል፤

  . . . በዚህ ትምህርት ቤት መልካም አስተዳደግና ትምህርትን ለማግኘት ለተ ሰበሰባችሁ ሁሉ በጠቅላላው ለኢትዮጵያ ሴቶች ልጆች ስለትምህርትና መልካም አስተዳደግ የምናስበውን ልንነግራችሁ እንወዳለን። ማመዛዘንና ማስተዋል የሚገኘው ከመልካም አስተዳደግና ከትምህርት ነው። ማመዛዘንም የሚያስንቁት ን ሥራዎች መናቅንና የሕሊና አሸናፊነትን አእምሮ ይሰጣል። . . . ኢትዮጵያ ከሴቶች ልጆችዋ የምትፈልገውን አገኘች ለማለት የሚቻለው እናንተ ተምራችሁ ለሴቶች የዕውቀት አባት ስትሆኑ ነው። ትምህርት ለሰው ልጅ በብዙ መንገድ ይጠቅማል። ሲታመሙ፣ ሲሰደዱ፣ ወዳጅ ሲከዳ፣ አእምሮ ሲበሳጭ፣ በአገር ጥቃት ሲገባ የማይለይ፣ አብሮ የሚኖር ዘመድ ነው። ይህን ስንላችሁ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሁለተኛ ድምፅ በሴቶች ጆሮ ይጮኻል። ይኸውም ሴት ልጅ ተምራ ምን ትሠራበታለች፤ ጥቂት ትምህርት ይበቃታል የሚል ነው። አንድ ወይን ተካይ በብዙ ድካም የተከለውን ወይን የሚሰጠው ፍሬ ሳይበስል ቢቆረጥ ለበላተኛውም መራራና ጐምዛዛ ይሆንበታል፣ የወይን ተካዩም ድካም ከንቱ ሆኖ ይቀራል። ወይ ኑ እስኪበስል የተጠበቀ እንደሆነ ደስታው የወይን ተካዩ ብቻ ሳይሆን ፍሬውን ለሚካፈሉ ሁሉ የሚደርስ ይሆናል። እንዲሁም እናንተ ትምህርት ወንድና ሴት እንደማይል አውቃችሁ ለፍሬ እንድትደርሱ ጠንክራችሁ መማር ነው። . . . ከመልካም አስተዳደግ ጋር ተባብሮ የቀረበላችሁን ትምህርት በንቃት መንፈስ የቀጠላችሁ እንደሆነ ከወንዶች ትክክል ሆናችሁ በፖለቲካ አስተዳደር፣ በወታደርነት፣ በአኤሮፕላን ነጂነትም ሆነ በሌላው ይህን በመሳሰለው ሥራ አገራችሁን ለማገልገል የመመረጥን ዕድል ታገኛላችሁ። ይህን የሚጠብቃችሁን መልካም ዕድል ለማግኘት በትምህርታችሁ ጠንክሩ።

  ዛሬ የሴቶች እኩልነት ጉዳይ ትልቅ ለውጥ ያስመዘገበ ጉዳይ ቢሆንም ንጉሠ ነገሥቱ ከላይ የጠቀስኩትን ቃል የተናገሩት ከስድሳ ሰባት ዓመታት በፊት መሆኑን ማጤን ያስፈልጋል። በዚያው ዓመት የካቲት ፩ ቀን ከየጠቅላይ ግዛቱ የመጡ የትምህርት ቤቶች ሥራ አስኪያጆች ግርማዊነታቸው ፊት ቀርበው በአገሪቱ ስላለው የትምህርት ሂደትና እድገት ሪፖርት አቅርበው ነበር። ግርማዊነታቸውም ከሰጡት ምላሽ ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፤

  ዘወትር የምናስበውና የምንሠራው የተማሪዎች ዕውቀት ከፍ እንዲል፣ ብዛታቸው እየበረከተ እንዲሄድና ትምህርት ቤቶች እንዲስፋፉ ነው። ይህ አሁን የተናገራችሁት የተማሪ ቤት ቁጥርና የተማሪዎች ብዛት በኢትዮጵያ ለ፲፭ ሚሊዮን ሕዝብ በቂ ነው ለማለት አያስደፍርም። የጊዜው የገንዘብ ችግርና የአስተማሪዎች በብዛት አለመገኘት የትምህርት ቤቶችን የተሟሉ ለማድረግ ባያስቸግር ኑሮ ስለትምህርት ቤቶች መስፋፋት በሚደረገው ድካም ከሕዝቡ አልጐደለም። ትምህርት ቤቶችን ከዚህ በበለጠ አኳኋን ለማስፋፋትና በተፋጠነ እርምጃም ለመሥራት እንዲቻል በበኩላችሁ እንድትጣጣሩ አደራ እንላችኋለን። እኛም እንረዳችኋለን።

  ጥቅምት ፯ ቀን ፲፱፻፶ ዓ . ም . ( ከሃምሳ ዘጠኝ ዓመታት በፊት ) ከልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል የነርሶች ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን አጠናቀው በዲፕሎም ለሚመረቁ ነርሶች ከተናገሩት ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፤

  የአገራችን ልጆች በማናቸውም ክፍል በትምህርት አድገውና በስለው ከማየት የበለጠ ለልባችን ደስታና ዕረፍት የሚሰጥ አይገኝም። ከትምህርት ምንጭ የተቀዳ ዕውቀት ሁሉ ለሰው ልጅ ደኅንነትና ለበጐ አድራጐት ብቻ ሳይሆን ለአገር ነፃነትም ዓይነተኛ ዓምድ ነው። የሰው ልጅ አሳቡ የሚጠቃለልለትና ሥራው የሚቃናለት ከትምህርት የሚገኘውን ዕውቀት ምርኩዝ አድርጐ በመሥራት ነው። እናንተም በክፍላችሁ ለሕሙማን ርዳታና መጽናኛ የሆነውን የአስታማሚነት ሥራ በመምረጣችሁ ከበጐ አድራጐቶች አንዱ በመሆኑ መልካም መ ር ጣችኋል። ነገር ግን ይህን ሙያችሁን ምቾት በሚገኝባቸው ሆስፒታሎች ብቻ ሳይሆን በሌላውም አስቸጋሪና አድካሚ በሆነ ሥፍራ ሁሉ እንድታውሉት የሚያስፈልግ ነው። ትምህርታችሁና ተግባራችሁ ይህንን እንድታደርጉ ያስገድዳችኋል። . . . የነርስነት ስም ብቻ ሳይሆን ግዳጆቹንም ጭምር የያዛችሁ መሆን አለባችሁ። ገና በአበባነቷ የተቀጨችው የተወደደች ልጃችን ልዕልት ፀሐይ ኃይለ ሥላሴ የነርስነት ትምህርቷን ጨርሳ የፍሎሬንስ ናይቲንጌልን ምሳሌ በመከተል የራሷን ምቾትና ተድላ ሳትፈልግ በልዩ ልዩ ሕመም የሚሰቃዩትን ወገኖቿን ለመርዳት ራሷን መሥዋዕት አድርጋ በቅንነትና በርኅራኄ ታጽናና ስለነበረች እናንተም በዚህ የርሷን ስም በተሸከመው ሆስፒታል የምትሠሩና የምትማሩ ሁሉ ምሳሌዋን በአእምሮአችሁ የተቀረጸ አድርጉት።

  አባባ ጃንሆይ ለመጻሕፍት ትልቅ አክብሮት እንደነበራቸውና የማንበብን ልምድ ያዳበሩ የመጻሕፍት ወዳጅ እንደነበሩ ብዙዎች መስክረውላቸዋል። ታኅሣሥ ፲፯ ቀን ፲፱፻፶ ዓ . ም . ወደሕዝብ መጻሕፍት ቤት ወመዘክር ሄደው ነበር . . .የአሜሪካ መንግሥትና ሕዝብ በስጦታ ያበረከ ቷ ቸውን አንድ ሺህ ልዩ ልዩ መጻሕፍት ለመመልከት ። በጉብኝቱም ወቅት የአሜሪካውን አምባሳደር ንግግር ተከትሎ ግርማዊነታቸው ከሰጡት መልስ ውስጥ የሚከተለው ቃል ይገኝበታል፤

  ያለትምህርት ሕይወት የለም እንደሚባለው ሁሉ ያለመጻሕፍትም የሊቃውንትን የአሳብ ፍሬዎች ለማኖርና ከትውልድ ወደትውልድ ለማስተላለፍ አይቻልም። የአሜሪካ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በስጦታ ስም የላካቸውን መጻሕፍት ለመጐብኘት ዛሬ በዚህ አዳራሽ በመገኘታችን ደስ ብሎናል። . . . ሕዝባችን በትምህርት ከፍ ወዳለው ደረጃ እንዲደርስ የምናደርገው ጥረት ካሉን ዓላማዎች ሁሉ ዋናው መሆኑን በመገንዘብ ስለገለጠልን መልካም አሳብና ሕዝባችንም እንዲጠቀምባቸው ስለተላኩልን መጻሕፍት እናመሰግናለን።

  የካቲት ፲፫ ቀን ፲፱፻፶፩ ዓ . ም . ( ከሃምሳ ስምንት ዓመታት በፊት ) ስድስት የአየር ኃይል መኰንኖች በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ግርማዊነታቸው ፊት ቀርበው ነበር። ስድስቱ ወጣት መኰንኖች የአየር ኃይል ፓይለቶች ነበሩ። ፓይለቶቹ ከራሳቸው አልፈው ሌሎች የጄት አብራሪዎችን ለማሠልጠን የሚያስችላቸውን ዕውቀት ለመገብየት ወደአሜሪካ ለመሄድ የተመረጡ፤ ከጉዟቸውም በፊት ግርማዊነታቸውን ለመሰናበት፣ የምክር ቃላቸውንም ለመቀበል የቀረቡ ነበ ሩ ። ግርማዊነታቸውም እንዲህ ብለዋቸው ነበር፤

  ወደአሜሪካ የምትላኩበት ተግባር ለጄት መብረር አስተማሪዎች እንድትሆኑ ለመሰናዳት ነው። . . . የአየር ኃይል ትምህርት ቤታችንን ስናቋቁም የተመኘነው ትምህርት አድጐ በአየራችን ላይ የሚበሩት አኤሮፕላኖች ሁሉ መላው ግዳጃቸው በአገራችን ልጆች ሲከናወን ማየት ነበረ። . . . የኢትዮጵያ አየር ኃይል እንደዚህ ባለ አጭር ጊዜ ውስጥ በጄት መብረር አስተማሪዎች ይኖሩታል ብለን ማሰብ ይቅርና ጄት አኤሮፕላን በቶሎ ወደዚህ ዓለም ክፍል የሚገባ አይመስለንም ነበር። . . . ጄት ማብረር መቻላችሁንና ከዚህም አልፋችሁ አስተማሪዎች ለመሆን የሚያስችላችሁን ዕውቀት ለመቀበል ወደወዳጅ አገር ስትሄዱ ማየታችንን ስናስተውለው የአየር ኃይላችን እንዲስፋፋ ያደረግነው ድካም ፍሬ መስጠቱን ስንመለከት ደስ ይለናል። . . . ሕዝባችን የሚረዳው ካገኘ ማናቸውንም ዓይነት ትምህርት ለመቀበል የሚያቅተው አለመሆኑን በሌላው ቀርቶ እናንተ . . . ያሳያችሁት . . . . በቂ ምስክር ሊሆን ይችላል። . . . በምትላኩበት አገር ተገኝታችሁ ሳትበርዱና ሳትቦዝኑ አሳባችሁን በጨዋታና በስንፍና ሳታባክኑ ትምህርታችሁን እንድትከታተሉ፣ እናንተም የምትኰሩበት እኛም የምንደሰትበት ምርት ውጤት ይ ዛችሁ እንድትመለሱ ተስፋ አድርገንባችኋል። ስለዚህ ግብረ ገብነታችሁና ትጋታችሁ ሥራ ወዳጅነታችሁም ለናንተ ብቻ ሳይሆን ለአየር ኃይላችንና ለሕዝባችን መገመቻ ስለሚሆን በ ሥራ ም ሆነ ከሥራ ውጭ በአኗኗራችሁ የምትመሰገኑበትን መንገድ መከተል አለባችሁ። . . . ይህ መሠረታዊ የሆነው ቁምነገር እየጐደለው ለገንዘብና ለንዋይ ሲል የሚያገለግል ሰው ማናቸውም ስጦታ ሊያስደስተው አይችልም። የገንዘብ ፍቅር ሰውን ማንም የሚገዛው ነው ለማሰኘት ይችላልና ከዚህ ተጠንቀቁ። 

  የዚያን ጊዜውን የምክር ቃ ል ተከታታይ ትውልዶች ሥራ ላይ ቢያውሉት ኖሮ ይህንን የስደትና የፍቅረ - ንዋይ ዘመን በድል አድራጊነት እንወጣው ነበር ብዬ አስባለሁ። ጥቅምት ፲፪ ቀን ፲፱፻፶፯ ዓ . ም . ከውጭ አገር ትምህርታቸውን አጠናቅቀው የተመለሱ አስራ ስምንት ወጣቶችን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ደግሞ የሚከተለውን ብለው ነበር፤

  . . . ደስታችን ፍጹም ሊሆን የሚችለው ካሁን በፊት ለከፍተኛ ትምህርት ወደውጭ አገር በላክናችሁ ጊዜ ተምራችሁ ስትመለሱ ባገኛችሁት ዕውቀት አገራችንን በሚጠቅም ሥራ እንድታገለግሉ ብለን የነገርናችሁን በሥራ ገልጻችሁ ስናይ ነው። . . . ስለኢትዮጵያ እድገት ዛሬ ላለብን ከባድ ሥራ እንደናንተ የተማሩ ልጆች የያንዳንዳችሁን አስር እጥፍ ብናገኝ እንዴት ደስ ባለን ነበር። በጠቅላላው የምንሰጣችሁ ምክር ታሪካችን ትልቅ ሥራችን ግን ትንሽ ሆኖ እንዳይገኝ በምትሠሩት ሥራ ሁሉ ጥንቃቄ እንድታደርጉ ነው።

  ማጠቃለያ ይሆነኝ ዘንድ አንድ ንግግራቸውን ልጥቀስ ና ላብቃ ። ይህንን ቀጥዬ የምጠቅሰውን ንግግራቸውን የዛሬው ኢትዮጵያዊ ትውልድ፣ በተለይም ደግሞ የዛሬዎቹ የኢትዮጵያ ምሁራንና ባለሥልጣናት እንዲሁም የሃይማኖት ሰዎች ቢያስተውሉት እንዴት መልካም ነበር ! መጋቢት ፳፫ ቀን ፲፱፻፶፩ ዓ . ም . ግርማዊነታቸው በትምህርት ቦርድ መሥሪያ ቤት ተገኝተው ትእዛዝ ሰጥተው ነበር። ትምህርትን በማስፋፋት በኩል ቦርዱና የትምህርት ሚኒስቴር ሊያከናውኑ ስለሚገባቸው አንዳንድ ሥራዎች መመሪያ ከሰጡ በኋላ ንግግራቸውን የደመደሙት እንደሚከተለው ነበር፤

  . . . ከሁሉም በፊት ተማሪዎቹ በግብረ ገብነት ረገድ መልካም አስተዳደግ እንዲያገኙ ይሁን። ተማሪዎቹ የአገራቸውን ታሪክና ልማድ ሳያውቁ የውጭ አገር ቋንቋ ብቻ ቢማሩም መሠረት የሌለው ይሆናል። ስለሀገራቸው ታሪክ ተጠይቀው መልስ ሲያጡ እነሱም ማፈራቸው የማይቀር ስለሆነ የዚህን ጉዳይ ቦርዱ እንዲነጋገርበት ይሁን። እንዲሁም . . . የአማርኛ አካዳሚ ጉባኤ ሊቃውንት እንዲቋቋም የተጠናና ያለቀ ጉዳይ ስላለ በሥራ ላይ እንዲውል ይሁን።

  አባባ ጃንሆይ በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካና በመላው ዓለም ሲታወሱ ይኖራሉ። ባሳደጓት ዋና ከተማ ውስጥ በሚገኘውና በግንባር ቀደምትነት ባቋቋሙት አኅጉራዊው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጽሕፈት ቤት ግቢ ውስጥ የ መታሰቢያ ሃውልት ቢነፈጉም ታላቅነታቸው በትውልዶች ልብ ውስጥ ሲያበራ ይኖራል። የቀደሙ መሪዎቻችንን የሚያከብር፣ ለኢትዮጵያ አንድነት ና ለታሪኳ የሚቆረቆር መንግሥት ሲመጣም አባባ ጃንሆይ ተገቢ የሆነውን የክብር ቦታቸውን እንደሚያገኙ አምናለሁ ። የልደት ቀናቸው ብሔራዊ ክብረ በዓል ሆኖ እንዲታወጅ ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ( እንደቀድሞው ) እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሕንጻም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስም እንዲሰየሙ እመኛለሁ ።

  እውነተኛ የሕዝብ አባት የሆነ የአገርና የሃይማኖት መሪ ቸሩ አምላክ ያድለን።

  አባባ ጃንሆይ፤ እግዚአብሔር ይስጥዎ።

  _______________________________________

  ሐምሌ ፳፻፱ ዓ . ም . │ July 2017 Washington, D C

  « Back to archive
 • Leave your comment

 • Name:
   
  Email:
  Comment   
  captcha
  Enter the code shown above: