• News

 • ኢህአዴግ ሆይ ተናገር!! | በጸሎት ፍ. በድሬቲዩብ 20 December 2017 | View comments

 • የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮምቴ ትልልቅ ውሳኔዎችን ያስተላልፈበታል የተባለው ስብሰባ ላይ እንደተቀመጠ ነው። የስብሰባውን መራዘም ላስተዋለ ከመቀመጥ ይልቅ ‘መወዘፍ’ የሚለው ቃል ይበልጥ ይገልጸዋል። ስብሰባው ስለምን እየመከረ ነው? ለምንስ የተራዘመ ሆነ? ጽ

  ማህበራዊ ድረገጾች ተመልከቱ። በስብሰባው ቃልአቀባዮች ተወርሮ ታገኙታላችሁ። እንደህዝብ ስልክ ሳንቲም ሲገባባቸው የሚጮሁት አንዳንድ ብሎገር ተብዬዎች እነለማ መገርሳን እየረገሙ፣ የእነአብዲ አስተዛዛኝ፣ መግለጫ ጸሐፊና አሰራጭ ሆነዋል። ሌላኛው መሠረቱን አሜሪካና አውሮፓ ያደረገው ክንፍ እነለማ መገርሳንና ገዱ አንዳርጋቸውን አቧድኖ ‘የበለው’ መዝሙሩን እያቀነቀነ ነው። ኢህአዴግ ግን ይህ ሁሉ ሲሆን ‘ ጥሪ አይቀበልም’ ብሎ፣ በሩን ከርችሞ በግምገማ እርስበርስ እየተሞሸላለቀ ነው። ኢህአዴግ በእኔና በቤተሰቤ፣ በሀገሬ ጉዳይ በዝምታ ታጥሮ፣ ራሱን ላልተጣራ ወሬና አሉባልታ አጋልጦ ስብሰባ የመቀጠሉ ፋይዳ ግን ለሰሚው ሁሉ ግራ ነው።

  ከሁለት ሳምንት በፊት የተካሄደውን የህወሓት ስብሰባ አስታውሱ። የእነወ/ ሮ አዜብ መታገድ ጭምር አስቀድሞ የነገረን ማህበራዊ ሚድያው ነው። ያው ሰዎቹ የሚሾሙትን፣ የሚያባርሩትን…ፈጽመው ለመግለጫ አደባባይ ሲወጡ ብዙ ሰው ባረጀው ዜናቸው ስቋል። አሁንም እየሆነ፣ እየተፈጸመ ያለው ተመሳሳይ ነው።

  የኢህአዴግ የበዛ ምስጢራዊነት ከመረጃ ዘመኑ ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም። ወቅታዊ መረጃ ያለው ህዝብ የነቃና መነሻና መድረሻውን የሚያውቅ የመሆኑ ጉዳይ አስረጅ አያስፈልገውም።በተቃራኒው መረጃ የተነፈገና ለአሉባልታ የተጋለጠ ህዝብ ስጉና ለሽብር የተጋለጠ መሆኑ እንዲሁ።

  በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም እንደፌስቡክ ባሉ ማህበራዊ ድረገጶች የሚጳፉ ነገሮች ሁሉ ትክክል አለመሆናቸውን፣ ሕዝብም የሚጳፈውን እንዳያምን ተማጵነው ነበር። ‘መማጰን’ ያልኩት ቢናገሩትም ሰምቷቸው ፊቱን እሳቸው ወደሚፈልጉዋቸው ሚድያዎች የሚመልስ ህዝብ እንደማይኖር አስቀድሞ የታወቀ ነበርና ነው። በዚህ ላይ ጠ/ ሚኒስትሩ ህዝብን ለፌስቡክ አሉባልተኞችና ራሳቸውን የሁሉ ጉዳይ አዋቂና ተንታኝ አድርገው የሾሙ ግለሰቦች ያጋለጠው እሳቸው የሚመሩት ግንባር መሆኑን ግን ረስተውታል። ይህ ግንባር ራሱን ሀሳብን በነጳ ለመግለጵ ነጻነት መከበር የታገለ፣ የተዋደቀ ጀግና አድርጎ ያስቀምጣል፣ ግን ምን ዋጋ አለው፤ ተግባሩ ግን ከወሬው እጅግ የዘገየ ነው።

  እርግጥ ኢህአዴግ አብሮት ባደገው በዚህ ባህርይው መረጃ ማፈኑ አዲስ ነገር የለውም። አዲሱ ነገር ሀገር እንዲህ በነውጥ በሚታመስበት፣ የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑ የዩኒቨርስቲ ወጣት ተማሪዎች ዘርና ጎሳ ለይተው በሚፋለሙበት አሳዛኝ ግዜ ላይ ጭምር የቀጠለ መሆኑ ነው።

  በአሁኑ የኢህአዴግ ስብሰባ እነለማ መገርሳ እና እነገዱ አንዳርጋቸው በአንድ ረድፍ፣ ህወሓቶች በሌላ ረድፍ መሰለፋቸው ተደጋግሞ እየተነገረ ነው። ኢህአዴግ ግን ስለመከፋፈሉም ሆነ አብሮ ስለመሆኑ እስካሁን ትንፍሽ አላለም። ይህ የበዛ ምስጥራዊነት ራሱ ለግንባሩም ቢሆን እየጠቀመው አለመሆኑን ማስታወስ ግን ይኖርብናል።
  ስብሰባው ሊጀመር ሰሞን የኢህአዴግ ጽ/ ቤት ሀላፊው አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በመንግሥት መገናኛ ብዙሀን ብቅ ብለው በስብሰባው ትልልቅ ውሳኔዎች እንደሚጠበቁ ሹክ አሉና በዚያው ጠፉ። ሰውየው፤ የስብሰባው አጀንዳ ምንድነው? ስንት ቀን ይቆያል? ካለፉት ስብሰባዎች የሚለየው በምንድነው ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ስለመስጠታቸው በግሌ የሰማሁት ነገር የለም።

  እናም ዛሬም ባለን ተባራሪ መረጃ መሠረት የተራዘመ ስብሰባው ቀጥሏል። ማህበራዊ ድረገጱም አለኝ በሚለው መረጃ ትንታኔ እንደተጠመደ ነው። እናም ነገሮች ቦክተው ከተጨማለቁ በሀላ ኢህአዴግ አለሁ ቢል እንደሀገር ጥቅም የለውም። እናም ኢህአዴግ ሆይ ምስጥራዊነቱ ይብቃህ! ተከሰትና ስለክፍፍልህም ሆነ አንድነትህ ተናገር!!!

   

  source DireTube

  « Back to archive
 • Leave your comment

 • Name:
   
  Email:
  Comment   
  captcha
  Enter the code shown above: