• News

 • ለነጋሶ 30ሺህ ብር? /የሁለቱ ዶክተሮች ወግ 12 February 2018 | View comments

 • ለነጋሶ 30ሺህ ብር? /የሁለቱ ዶክተሮች ወግ

  ለነጋሶ 30ሺህ ብር? /የሁለቱ ዶክተሮች ወግ

  ዶ/ር ነጋሶ 30 ሺህ ብር እንዲከፈላቸው የዶ/ር ዓብይ አሕመድ መሥሪያ ቤት ወስኗል የሚለው ዜና ሰሞኑን መነጋገሪያ ነበር፡፡የዶ/ር ዓብይ መሥሪያቤት ማለት ኦሕዴድ ነው፡፡ለ10 ቀናት በአዳማ ጉባኤ ያካሄደው ኦሕዴድ ለዶክተሩ ሕክምናና መኪናም እንዲያገኙ ይደረጋል ብሏል፡፡3ሺ ብር በማይሞላ የጡረታ ገንዘብ፣ ኑሯቸውን ሲገፉ የነበሩት ዶክተር ነጋሶ አሁን 30ሺህ ብር ወርሃዊ ደመወዝ ያገኛሉ፡፡ይህ ትልቅ ተግባር ነው፡፡ግን ሒደቱ ሕጋዊ ነው ወይ…? ኦሕዴድስ ይህንን ለማድረግ ያስገደደው ሞራል ነው ወይስ ሕግ? የሚለው ያከራክረናል፡፡

  ነጋሶ ለምንና መቼ ከኢሕአዴግ/ኦሕዴድ ወጡ?
  ዶ/ር ነጋሶ በሽግግሩ ወቅት ለአንድ ዓመት የሰራተኛና ማኅራዊ ጉዳይ በኋላም የማስታወቂያ ሚኒስትር ነበሩ፡፡ ከዚያም የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው በአሁኑ ሕገመንግሥት ላይ ፊርማቸውን አስቀመጡ፡፡በዚህ ሥልጣናቸውም እስከ መስከረም 28-1998 ዓ.ም. ድረስ ቆዩ፡፡በዘመኑ የነበረው የሕወሓት ክፍፍል ገፊ ምክንያት ሆነና ኢሕአዴግንና ነጋሶንም ሆድ አባባሳቸው፡፡

  ነጋሶን በአንጃው ደጋፊ መጠርጠር ተጀመረ፡፡የሁለቱን ጀኔራሎች (የፃድቃንና የአበበ) መነሳትም ሕገወጥ ነው ብለው ዶ/ር ነጋሶ በመጠየቃቸው ከሊቀመንበሩ ጋር አላስማማቸውም፡፡ከኢሕአዴግ የመልቀቃቸው ዋና ምክንያት ግን አይደለም፡፡

  በ1993 ዓ.ም ከሰኔ 10 ጀምሮ የኢሕአዴግ ም/ቤት ጉባኤ ተካሂዶ ነበር፡፡በወቅቱ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ነበሩ-ጉባኤውን የመሩት፡፡በጉባኤው ላይም አቶ መለስ ኢትዮጵያ የምትከተለው ርዕዮት ነጭ ካፒታሊዝም መሆኑን፣አገሪቱ ከግሎባላይዜሽን ምን እንደምትጠቀም፣ እንደ ሞዴል የምትከተላቸው ሃገራትም እነ ኮሪያ እንደሆኑ አብራሩ፡፡

  ይህ ዶ/ር ነጋሶን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ የም/ቤቱን አባላት አበሳጨ፡፡ደ/ር ነጋሶ አቶ መለስን አታለኸናል አሏቸው፡፡እኛ ኢሕአዴግን ያመንው አብዮታዊ ዴሞክራሲን የሚያራምድ ድርጅትና ለላብ አደሩ የቆመ መስሎን ነው፡፡እንዴት እንዲህ ይደረጋል ሲሉ ተከራከሩ፡፡አቶ መለስም ለወዛደር መቆም የሚባለው ጉዳይ ከ1983 ወዲህ የኢሕአዴግ መርህ መሆኑ እንዳበቃለት ተናገሩ፡፡ይህ የሆነው ሐሙስ ቀን ሰኔ 14-1993 ዓ.ም ነበር፡፡

  በዚያኑ ዕለት ማታ በኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ተካሄደ፡፡በጉባኤው ላይ የሙሰኛ ባለሥልጣናት ጉዳይ ተነሳ፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ‹‹የወንድምህን ልጅ ከአሜሪካ አምጥተህ በዲንሾ ውስጥ አስቀጥረኻል፤ልጅህም ከደምቢ ዶሎ መጥታ ኦሮሚያ ፋይናንስ ቢሮ የተቀጠረችው ባንተ ምክንያት ነው›› የሚል ክስ ቀረበባቸው፡፡ተበሳጩ፡፡

  ደምቢ ዶሎ ልጅ እንደሌላቸውና የወንድማቸውን ልጅም ያመጡት እነ ሶፊያን መሆናቸውን ቢከራከሩም የሚያሳምኑት ሰው አልተገኘም፡፡ኢሕአዴግ በርዕዮተ-ዓለም አታለለኝ ብለው ሲበግኑ የከረሙት ዶ/ሩ አሁን ደግሞ በኒፖቲዝም (ሙስና) በመወንጀላቸው ተቃጠሉ፡፡ሌሊቱን እንቅልፍ ሳይተኙ ሲንጎራደዱ አደሩ፡፡

  ጠዋት ለባለቤታቸው አማከሩ፡፡‹‹ኢሕአዴግን ልለቀው›› ነው አሏቸው፡፡ሚስትዮዋ ፈቀዱ፡፡የኢሕአዴግ ም/ቤት ስብሰባ ቀጥሏል፡፡ዶ/ር ነጋሶ አዳራሹ ውስጥ የተገኙት ግን ለስንብት መሆኑን ማንም አያውቅም፡፡ድንገት እጃቸውን አውጥተው ‹‹እኔ የኢሕአዴግ አካሔድ ስላልተስማማኝና ሕሊናዬ ስላልፈቀደ ከዛሬ ጀምሮ ከኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚም ሆነ ም/ቤት ወጥቻለሁ›› አሉ፡፡ዕለቱ አርብ ሰኔ 15-1993 ዓ.ም ረፋድ ላይ ነበር!!

  እነሆ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ኢሕአዴግና ነጋሶ ሰማኒያ ቀደዱ፡፡የፕሬዚዳንት ዘመናቸው ሊጠናቀቅ ግን ሁለት ወር ይቀረው ነበር፡፡ነሀሴ 1993 ዓ.ም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ስድስት ዓመት ሞላ፡፡ሥልጣናቸው አለቀ፡፡ መስከረም 28-1994 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ቤተመንግሥቱንም በትረሥልጣኑንም ለአቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ አስረክበው ወጡ፡፡
  የአዋጇ ነገር፣…

  ዶ/ር ነጋሶ በቀድሞ ፕሬዚዳንትነታቸው ሊያገኙት የሚገባቸውን ጥቅም የገደበችውና የደነገገችው አዋጅ 255/94 ትሰኛለች፡፡አዋጇ ‹‹የቀድሞ ፕሬዚዳንት ከፖለቲካ ወገንተኛነት መገለል አለበት፡፡ወገንተኛ ከሆነ ጥቅማ ጥቅሙ ይቋረጣል ትላለች››፡፡አዋጇ የጸደቀችው ደግሞ መስከረም 28-1994 ሰኞ ጠዋት (ነጋሶ ከሰዓት ሥልጣን ከማስረከባቸው በፊት ማለት ነው)!!

  አዋጇ በሁለት ምክንያት ተቀባይነት የላትም፡፡አንደኛ የወጣችበት ዕለት ሕገወጥ ነው፡፡ይቺን አዋጅ ለማውጣት ፓርላማው ሰኞ ጠዋት ነበር የተሰበሰበው፡፡ይህ ስብሰባ ሕገወጥ ነው፡፡በዓመቱ መጀመሪያ ወር (ማለትም መስከረም) የመጨረሻ ሰኞ በሁለቱ ም/ቤቶች የጋራ ስብሰባ በፕሬዚዳንቱ ሞሽን ሊከፈት የሚገባው ፓርላማ፣ ጠዋት ላይ ተሰባስቦ ከላይ የተጠቀሰችውን አዋጅ አወጣ፡፡

  ሁለተኛ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት አንድ ፓርላማ የገባ አባል ውግንናው ለመረጠው ሕዝብ፣ለሕገ-መንግሥቱና ለኅሊናው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ዶ/ር ነጋሶም ሆነ የትኛውም ፕሬዚዳንት ግን ፖለቲካዊ ውግንና ማድረግን በአዋጅ ተከለከለ፡፡እርሳቸው የኦሕዴድ አባል (ለኦሕዴድ በመወገናቸው) ምክንያት ፕሬዚዳንት እንደሆኑ ግን ተዘንግቷል፡፡

  የሆነው ሆኖ ሥልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ እስከ ሐምሌ 1-1997 ዓ.ም ድረስ ቤትም መርቸዲስና ላንድ ክሩዘርም ነበራቸው፡፡ሕክምናም ያገኙ ነበር፡፡ አትክልተኞች፣ የቤት ሰራተኞች፣ የቤቱ አስተዳዳሪና ቦዲ-ጋርዶች፣ግቢያቸውን የሚጠብቁ የፌደራል ፖሊስ አባላትም ተመድበውላቸውም ነበር፡፡ሆኖም በ1997ቱ ምርጫ በግላቸው ተወዳድረው ፓርላማ በመግባታቸው ለአራት ዓመታት ከመንግሥት የሚያገኙት ጥቅም ተቋረጠ፡፡ሠራተኞቻቸው ተበተኑ፡፡መኪኖቻቸውን ተቀሙ፡፡ቤቱ ብቻ ቀራቸው፡፡

  የሁለቱ ዶክተሮች ወግ…
  ባለፉት 13 ዓመታት ዶ/ር ነጋሶ የደረሰባቸውንና ያሳለፉትን በሙሉ ከዕለታት በአንዱ ቀን ዶ/ር ዓብይ ለተባሉት የኦሕዴድ ጽ/ቤት ኃላፊ ዘረዘሩ፡፡ሁለቱ ዶ/ሮች ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ተነጋገሩ፡፡ዶ/ር ነጋሶ ጥቅማቸውን ለማስመለስ ኦሕዴድ ሊያግዛቸው ይችል እንደሆነ ጠየቁ፡፡ዶ/ር ዓብይም ተነጋግረን አሳውቅዎታለሁ ብለው ወደ ጽ/ቤታቸው ተመለሱ፡፡

  ከዚያም በጥር-2010 የመጨረሻ ሳምንታት ላይ ኦሕዴድ በማዕከላዊ ኮሚቴው አማካኝነት ለስብሰባ ተቀመጠ፡፡ውሳኔም አሳለፈ፡፡ለነጋሶ መኪና እንዲሰጣቸው፤30ሺህ ብር ወርሃዊ ደሞዝ እንዲከፈላቸው፣ከዚያ በፊትም ጠቀም ያለ የኪስ ገንዘብ እንዲሰጣቸው በአብላጫ ድምጽ ወሰነ፡፡ውሳኔው ተግባራዊ ሆነ፡፡

  ዶ/ር ነጋሶ ከኦሕዴድ የተፈቀደላቸው ጥቅማ ጥቅም የፌደራል መንግሥቱ የከላከላቸውን ነው፡፡ ኦሕዴድ ይህንን ሲያደርግ አዋጅ 255/94ን ስላለመጣሱ የሕግ ባለሙያዎች ሊከራከሩበት ይችላሉ፡፡ይህ ውሳኔ በ1994 ሲወሰን ግን ኦሕዴድ አንዱ ወሳኝ ነበር፡፡ዛሬ በጓሮ በር ለምን ይህንን መንገድ እንደመረጠ የኦሕዴድ እግዜር ነው-የሚያውቀው፡፡ዶ/ር ነጋሶም የኔ ጉዳይ ከድርጅት በላይ ነው፤ጥቅሜን የቀማኝ የፌደራሉ ፓርላማ ነው ብለዋል፡፡

  የሆነው ሆኖ ነጋሶ ይገባቸዋል፡፡የአገር መሪ ሆኖ ስልጣን ከለቀቀ በኋላ በጡረታ ገንዘብ ብቻ የኖረ፣ተቸግሮ በአውቶቡስ የሄደ፣ለሕክምናና ለቀለብ ከልጁና ከሚስቱ ዘመድ ገንዘብ እየተበደረ ሕይወቱን ለ13 ዓመታት የገፋ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ በመሆን ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ይመዘገባሉ፡

  « Back to archive
 • Leave your comment

 • Name:
   
  Email:
  Comment   
  captcha
  Enter the code shown above: