• News

 • የደቦ ፍርድና የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ 15 August 2018 | View comments

 •  

  ዕለቱ ሰኞ ቀኑ ደግሞ ነሐሴ 7 ቀን 2010 ዓ.ም.፡፡ ጉዞ ከድሬዳዋ አዲስ አበባ ሲሆን፣ በመኪናዋ ውስጥ አራት ሰዎች ተጭነዋል፡፡ ሳይረፍድ የተነሳው የመኪናዋ ሾፌር አዲስ አበባ ደርሶ ለመመለስ ካለው ጉጉት የተነሳ፣ ለተሳፋሪዎቹ ይኼንኑ እያወራ መኪናዋን ከፍጥነቷ ልክ በላይ ያከንፋታል፡፡

  መኪናዋ አዋሽ አርባን እስከምትሻገር መንገዱ በሙሉ ሰላም ነበር፡፡ ይሁንና መኪናዋ ከአዋሽ አርባ ብዙም ሳትርቅ የጉዞውን ድባብ የለወጠ ክስተት ተፈጠረ፡፡ መንገድ በማቋረጥ ላይ የነበሩ አዛውንት በመኪናዋ ይገጫሉ፡፡ ሾፌሩም ፍጥነቱን መቆጣጠር ስላልቻለ ሊያድናቸው አልቻለም፡፡

  ይህ ግን በአገሪቱ የተለመደና ሲሰማ የቆየ የትራፊክ አደጋ ክስተት ብቻ ሆኖ አልቀረም፡፡ ይልቁንም በአገሪቱ እየተንሰራፋ የመጣውን የመንጋ ፖለቲካና የደቦ ፍርድ ሰለባ ከሆኑ ጥፋቶች መደብ ገባ እንጂ፡፡

  በሥፍራው ከቆይታ በኋላ የተገኘው የትራፊክ ፖሊስ ሾፌሩን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወስዶ በቁጥጥር ሥር ቢያውለውም፣ በሕግ ከለላ ሥር መሆኑ ከጥቃት ሊያድነው አልቻለም፡፡ የትራፊክ ፖሊሱን ተከትለው የመጡ የአካባቢው ወጣቶች በፖሊስ ላይ ጥቃት ሰነዘሩ፡፡ አደጋ ያደረሰው ግለሰብ ለሕግ ከሚቀርብ እኛ እንቅጣው በማለትም በንዴት መንፈስ መኪናዋን ሰባበሩ፡፡ አደጋ ያደረሰው ግለሰብም ድብደባ ተፈጸመበት፡፡

  በመቀጠልም የመኪናዋን ቁልፎች ከፖሊስ በመቀማት ማንም ከቦታው እንዳይንቀሳቀስ ማገዳቸውን በሥፍራው የነበረችና በአጋጣሚ በምታውቀው ሾፌር ዕርዳታ መኪና ቀይራ አዲስ አበባ የገባች ወጣት ለሪፖርተር አስረድታለች፡፡

  ይህ ከሕግ ውጭ የሚሰጥ የደቦ ፍርድ ምክንያት በርካቶች ሰለባ ከሆኑባቸው ክስተቶች አንዱ አብነት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን በየቀኑ መስማትም የተለመደ ሆኗል፡፡

  በተመሳሳይ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦኤምኤን) ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃዋር መሐመድን ለመቀበል እሑድ ነሐሴ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. በሻሸመኔ በወጡ በርካታ ግለሰቦች መሀል ቦምብ ይዞ ተገኝቷል ተብሎ የተጠረጠረን አንድ ግለሰብ፣ በሥፍራው የተሰበሰቡ ወጣቶች በመጠቋቆም በድንጋይ ደብድበው መግደላቸውና ዘቅዝቀው መስቀላቸው በርካቶችን ያሳቀቀና አንገት ያስደፋ ነበር፡፡

  ከሻሸመኔው ክስተት አንድ ቀን አስቀድሞ በምሥራቅ ወለጋ ወሊገልቴ በተባለች የገጠር ቀበሌ ውስጥ፣ ሁለት ግለሰቦች በተሰበሰቡ ወጣቶች ጥቃት ተሰንዝሮባቸው መሞታቸውም ተሰምቷል፡፡ እነዚህ ሁለት ሟቾች በአካባቢው ከ30 ዓመታት በላይ የቆዩና ከማኅበረሰቡ ጋር ተዋህደው የኖሩ ቢሆንም፣ እንደ ባይተዋር የደቦ ሰለባ ከመሆንና ከመሆንና ያለገላጋይ ተደብድበው ከመገደል አላተረፋቸውም፡፡

  ሌላም በርካታ አብነቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ወደ አዲስ አበባ ይመጡ የነበሩትን የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ጉብኝት ለመዘገብ፣ ሐምሌ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ የነበሩ የድሬዳዋ መገናኛ ብዙኃን የጋዜጠኞች ቡድን አባላት፣ ሰላይ ናችሁ በሚል ፍረጃ በማይታወቁ ወጣቶች ተደብድበው የቡድኑ ሾፌር ሕይወቱ ማለፉ ይታወሳል፡፡ ሁለት የቡድኑ አባላትም ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ደርሶባቸው ነበር፡፡

  እንዲህ ዓይነቱ ክስተት በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ በአገሪቱ በስፋት እየታየ ያለው የመንጋ ፖለቲካና የደቦ ፍርድ ሕይወት መቅጠፉ እንዳለም የዜጎችን ንብረቶች ቀምቶ መከፋፈልንም ያካተተ ነው፡፡

  እሑድ ነሐሴ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ባህር ዳር ከተማ ውስጥ ወደ ትግራይ በቆሎ ጭኖ እየሄደ ነው የተባለ አንድ ተሸከርካሪ በማስቆም፣ ወጣቶች በቆሎውን በማውረድ በአካባቢው ለሚገኙ ሰዎች አከፋፍለዋል፡፡

  እነዚህ ድርጊቶች ባለፉት አራት ዓመታት በአገሪቱ በነበረ ከፍተኛ ተቃውሞና ብጥብጥ ምክንያት ከደረሱ የንግድ ተቋማትና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መቃጠልና መዘረፍ፣ ብሎም የሰዎች ሕይወት መጥፋትና የአካል መጉደል አንፃር እንደሚለዩ፣ በከፍተኛ የፖለቲካና የሕግ ማስተካከያዎች ካልተፈቱ ወደ መንግሥት አልባነት ሊመሩ የሚችሉ እንደሆኑ የሕግና የፖለቲካ ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡

  አገሪቱ ከችግር አዙሪት በመውጣት ላለፉት የፖለቲካ አለመረጋጋቶች መፍትሔ የምትሰጥበት ዕድል አግኝታ ሳለች፣ የለውጥ ዕርምጃዎች እየተወሰዱና አገራዊ ዕርቅና መግባባት እየመጣ ነው በሚባልበት ወቅት መከሰታቸውም፣ በኢትዮጵያዊነት እሴቶች ላይ ሳይቀር ጥያቄዎች እንዲነሱ እያደረጉ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መካነ ጥናት ውስጥ የሚያስተምሩትና በግጭትና ግጭት አፈታት ላይ የምርምር ሥራቸውን የሚያተኩረው ደመቀ አቺሶ (ዶ/ር) እንዲህ ዓይነት ክስተቶች በሽግግር ውስጥ ባሉ አገሮች የሚከሰቱ መሆናቸውን በመጠቆም፣ የሕግ የበላይነትን በማስፈን በቁጥጥር ሥር ካልዋሉ እየተከሰቱ እንዳሉት ዓይነት ለመስማት የሚቀፉ ወንጀሎች እንዲፈጸሙ ሊያደርጉ ይችላሉ ይላሉ፡፡

  እንደ እሳቸው ምልከታ፣ የዚህ ችግር ምንጮች በፌዴራልና በክልል መንግሥታት መካከል ያለው ግንኙነት መላላቱና ክልሎች ራሳቸውን አጥረው አትድረሱብን እስከማለት መድረሳቸው፣ በተጨማሪም የፌዴራል መንግሥት መዳከም ናቸው፡፡

  ‹‹መንግሥት ቢያንስ በክልሎች የማስተባበር ሥራ መሥራት ካልቻለ ብዙ ቀውሶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ በተለይ በኢሕአዴግ ውስጥ የተፈጠረው ክፍተት፣ እየጠነከሩ የመጡ ቡድኖች ችግሮችን መፍጠር እንዲችሉ አግዟቸዋል፤›› የሚሉት መምህሩ፣ ኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ የምትታወቅባቸው እሴቶች መቻቻል፣ መተባበር፣ መፋቀር፣ መተሳሰብ መሆናቸውን፣ እነዚህን እሴቶች የማይገልጹ ድርጊቶች መታየታቸው፣ ‹‹ዕውን ኢትዮጵያውያን ነን ወይ፣ እስከዛሬስ ዕውን ተቻችለን ኖረናል ወይ፤›› ብለን መልሰን ራሳችንን እንድንጠይቅ የሚያደርጉ ክስተቶች እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡

  ስለዚህም ምንም እንኳን ከማኅበረሰቡ በላይ ትልቁን ሚና መጫወት ያለበት መንግሥት ቢሆንም፣ ሕዝቡ ትልቅ ኃላፊነት አለበት ይላሉ፡፡ እንደ እሳቸው ዕይታ ዴሞክራሲ ከመብት ጋር ብቻ ተቆራኝቶ መነገሩ ትልቅ ክፍተት የፈጠረ ሲሆን፣ ይኼንን ጉድለት ለመሙላት ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡ በተለይ ማኅበረሰቡ፡፡

  ‹‹በአሁኑ ጊዜ መንግሥት፣ መንግሥት የሚባልበት ጊዜ አይደለም፡፡ በግልጽ ጠንክሮ የወጣ ኃይልም የለም፡፡ የክልልና የመንግሥት ኃይሎች በጋራ እየሠሩ አይደለም፡፡ የፌዴራል መንግሥትም ይፍጨረጨራል እንጂ በተግባር የለም፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ማድረግ ያለበት ከጠባቂነት መንፈስ ወጥቶ እንዲህ ዓይነት አስፀያፊ ነገሮች እንዳይደገሙ በርትቶ መሥራት አለበት፤›› ሲሉም ያሳስባሉ፡፡

  በዚሁ ጉዳይ ላይ ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉ አንድ የሕግ ባለሙያ ደግሞ፣ ሕግና ሥርዓት አልባነት ቀላል ከሆነውና ከወንጀል ሕግ ጥሰት ዕይታ በላይ ምልከታ የሚያስፈልገው እንደሆነ ገልጸው ከፖለቲካ፣ ከማኅበረሰብና ተያያዥ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር መታየት እንዳለበት በመግለጽ የሕግን መኖር በራሱ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ክስተቶች እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡

  ‹‹ምንም እንኳን መነሻ የሆኑ ምክንያቶች ሊኖሩ ቢችሉም፣ እንዲህ ዓይነት ድርጊት በምንም ዓይነት ሁኔታ ልክ ነው ሊያስብሉ የሚችሉ አይደሉም፡፡ የሰዎች ደኅንነት ጥያቄ ውስጥ መውደቅ የለበትም፡፡ ሕግና ሥርዓት አለ እስከተባለ ድረስ እንዲህ ዓይነት ተግባራትን በትዕግሥት ማለፍ አይቻልም፤›› ይላሉ፡፡

  ከዚህ ባለፈ ግን መንግሥት በዝምታ የሚያልፍና ድርጊቶቹን የሚታገስ ከሆነ፣ በመንግሥት ኃላፊነት ላይ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ የመንግሥት ግዴታ የሕግ ተፈጻሚነትን ማረጋገጥ ሲሆን፣ በአንድ አካባቢ ሕግ የሚሠራበት በሌላው ደግሞ የማይሠራበት አግባብ መኖር የለበትም ባይ ናቸው፡፡

  መንግሥት በእንዲህ ዓይነት ሒደቶች የሚያቅተው ከሆነና እየተደጋገሙ የመጡት ክስተቶች በቁጥጥር ሥር መዋል ካልቻሉ አገሪቱን ወደ ከፋ አደጋ ሊከታት እንደሚችል የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ደመቀ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡

  ‹‹ይህ ሙሉ በሙሉ ሕግ አልባነት ነው፤›› የሚሉት መምህሩ፣ የኃይል ማዕከሉ ካልተለየና ትዕዛዙ ከየት እንደሚመነጭ በግልጽ የተበጀ መስመር እስከሌለ ድረስ አገሪቱ ወደ ዘመነ መሳፍንት እንደማትመለስ ዋስትና የለም ብለዋል፡፡

  ‹‹መንግሥት ሲፍጨረጨር ነው እንጂ የሚታየው ዕርምጃ የመውሰድ አቅሙ ከእጁ የወጣ ይመስላል፡፡ የፌዴራል መንግሥት እጆቹ ካጠሩና ማስተዳደር ካቃተው ሁሌም የሰው ደኅንነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ የፖለቲካ ትርክት የማያውቁና እንጀራ ጠግበው ያልበሉ ድሆች እየሞቱ እንዲሁ አገር እንገነባለን የሚል ቡራ ከረዩ ምንም አይገባኝም፤›› ሲሉም ይነቅፋሉ፡፡ ስለዚህ መንግሥት የተበታተኑ የኃይል ማዕከላትን ወደ አንድ ማምጣት ይገባዋል ይላሉ፡፡

  ‹‹የፌዴራል መንግሥት ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ ብዙ ነገሮች ከእጃችን ካመለጡ በኋላ እንዳይፀፅተን እሠጋለሁ፤›› ሲሉም ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ያለበለዚያ ወደ መንግሥት አልባነት ልንሸጋገር እንችላለን፤›› ይላሉ፡፡

  ይህ የደቦ ፍርድ ባለፉት አራት ዓመታት ሲታይ የነበረ ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ‹‹ፀጉረ ልውጥ›› በማለት የተናገሩትን ንግግር በማስታወስ፣ እሳቸውን የሚወቅሱ አካላትም በማኅበራዊ ሚዲያው ታይተዋል፡፡

  ምንም እንኳ በዚህ አባባል ላይ የተለያዩ ምልከታዎች ቢኖሩም፣ ንቃተ ህሊናቸው ዝቅተኛ የሆኑ ወጣቶች በስሜት ተገፋፍተው ዕርምጃ መውሰዳቸው ስለማይቀር ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ የሚገልጹ አሉ፡፡ በቅርቡ በባህር ዳር ከተማ የኤችአይቪ ጥናት ሲያደርጉ በነበሩ ባለሙያዎች ተሽከርካሪ ላይ የተፈጸመውን ቃጠሎ እንደ ምሳሌም ያነሳሉ፡፡ ወጣቶቹ ፀጉረ ልውጦች በማለት ነበር ድርጊቱን የፈጸሙት፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ‹‹በታዳጊ ክልሎች አዳዲስ ኃይሎች አዳዲስ ፀጉረ ልውጥ ሰዎች እየተንቀሳቀሱ የሚያደራጁት ኃይል ካለ ሥርዓቱ ብቻ ሳይሆን ወጣቶች ቆቅ ሆነው እንዲጠብቁ፤›› ሲሉ ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡

  ይሁንና ይህ ንግግራቸው ሥጋት ላይ የጣላቸው አካላት ለጠቅላይ ሚኒስትር ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ ‹‹ፀጉረ ልውጦች የተወሰኑ የአንድ ብሔር ተወላጆች ናቸው ብሎ ማሰብ በመሠረቱ የተሳሳተ ነው፤›› ሲሉ ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹የትግራይ ሕዝብ ኦሮሚያ ወይም አማራ ክልል ውስጥ ፀጉረ ልውጥ ሊሆን አይችልም። ፀጉረ ልውጥ ያልኩት በፍፁም አንድን ቡድን በሚገልጽ መልኩ ሳይሆን፣ የሚሰማሩ ኃይሎች ስለነበሩ መረጃው ስላለኝ ነው እንጂ የሆነ ቡድን ፀጉረ ልውጥ ሌላኛው ደግሞ ንፁህ ለማለት አይደለም፤›› ብለው ነበር፡፡

  ይሁንና አሁን በአገሪቱ እየታየ ያለው በምንም ዓይነት ምክንያትና መለኪያ ተቀባይነት የሌለውና ሊወገዝ የሚገባው ተግባር መሆኑን በርካቶች የሚስማሙበትና በተለያዩ መንገዶችም ሲገልጹት የቆዩት ሐሳብ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን እንደ ኢትዮጵያውያን የሚገለጹባቸው እሴቶች እየተናዱ ሲመጡ አገሪቱ እንደ አገር አደጋ ላይ ልትወድቅ እንደምትችልም የሚያሳስቡ አልጠፉም፡፡

  በብሩክ አብዱና በዳዊት እንደሻ

  Source: .ethiopianreporter.com

  « Back to archive
 • Leave your comment

 • Name:
   
  Email:
  Comment   
  captcha
  Enter the code shown above: