• News

 • "የነፍስ ጨለማን የሚያበራው !! " ለማ መገርሳ ! 16 August 2018 | View comments

 • 
  
  አለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)

   

   (ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው !!) በማለት የለውጡን ባቡር ከአብይ አህመድ ጋር የሚዘውረው 
   ለማ መገርሳ .......መጣ እያገሳ...!  - በሚል ዜማ አድናቂዎቻቸው ያቀነቅኑላቸዋል :: ሆኖም ግን 
  ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ለማ መገርሳን ጨምሮ የአንድነት አቀንቃኞቹ የልኡካን ቡድን ሜኖሶታ ኢትዮጵያውያኖቹ የተሰባሰቡበት እስቴድዮም ሲገቡ በህልም አለም የሚኖሩ የአንድነቱ እንደመር ደወል ያልቀሰቀሳቸው ገና ከንእንቅልፋቸው ያልተነሱ ሰዎች አጋጥማዋቸው ነበር :: የሚናገሩበትን ብሔራዊ የሐገሪቱን ቋንቋ እንዲቀይሩና በአፋን ኦሮሞ እንዲናገሩ ሲጠየቁ :: እሽ ቀጥየ በአፋን ኦሮሞ እናገረለሁ አሉ ::
   ብልህ እና አስተዋይ ፣ የረጅም ጉዞ የለውጥ አቀንቃኙ ኦቦ ለማ መገርሳ ግን አንድ ሐሳብ በውስጣቸው ሲመላለስ ያዳመጡ ይመስላሉ :: የመነጋገሪያውን ሰገነት ላይ እንደቆሙ ቁልቁል ወደህዝቡ አስተዋሉ ::
  
  ትዝብታቸው ለኔ እንደገባኝ ከሆነ  የአንድ ሐገር ህዝብ በጋራ እንዲጎለብት ካስፈልገ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች አንድ ላይ ሲዋሐዱ እና በአንድ ጥላ ስር መሰባሰብ የሚያስተሳስረን የጋራ ታሪካችን ኢትዮጵያዊ ሰንሰለት መሆኑን መረዳት እንዳለብን እንዲህ በማለት አስገነዘቡን ::
  
  "አንድ ስንሆን ብቻ እናምራለን። በልዩነት አንድ ስንሆን ውበታችን ይደምቃል። መከፋፈል ውርደት እንጅ ክብር የለውም። በእውነት ሀገራችንን ለመለወጥ ከሆነ አንድነታችንን ማጠናከር አለብን። ኦሮሞነት ለኢትዮጵያ ስጋት ሳይሆን ውበት ነው፤ ኃይልና ጉልበት ነው። አማራነት ለኢትዮጵያ ስጋት ሳይሆን ውበት ነው፤ ኃይልና ጉልበት ነው። ሶማሌነት ለኢትዮጵያ ስጋት ሳይሆን ውበት ነው፤ ኃይልና ጉልበት ነው። ሌላውም እንዲሁ። እኛ ኢትዮጵያውያን የትም ብንሄድ ማንነታችን አይሰለብም። ይህ ነው የኢትዮጵያዊነት ሱስነት። የኢትዮጵያ የጥንካሬ ምንጭ አንድነት "አንድ ስንሆን ብቻ እናምራለን። በልዩነት አንድ ስንሆን ውበታችን ይደምቃል። መከፋፈል ውርደት እንጅ ክብር የለውም። በእውነት ሀገራችንን ለመለወጥ ከሆነ አንድነታችንን ማጠናከር አለብን። ።" ሲሉ ተደመጡ ::
  
  በእርግጥ ለማ ትክክል ናቸው ለአንድ ሐገር መሰረት ቋንቋ ባህል ሐይማኖት ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ እና የጋራ ታሪክ አስፈላጊ ነው :: በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ምናልባት በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ተቀላቅለው ተወራርሰውና ተዋህደው ስልጣኔ እና ታሪካቸውን ዛሬ ያለውን የኢትዮጵያ ህዝብ ምስል እንዲከሰት ምክኒያት ሆኖ ይሆናል :: 
  
  ብሔራዊ አላማ ሊኖረን ይገባል ከምንጏተተው ባንድራ ይልቅ የዳር ደንበራችን መከበር የህዝባችን መብት መጠበቁን የደህነታችን ጉዳይ እና የኢኮኖሚና የፓለቲካችን ጉዳይ እጅግ በጣም ያሳስበናል ::
  
  በሆነ ባልሆነው መጏተት አይኖርብንም :: ማንም የመንፈስ ስብራት እንዲደርስበት አንፈልግም :: ማንም ፎካሪ ሊሆን አይችልም :: አንዱ በአንዱ እሬሳ ላይ ቆሞ የሚፎክርበትን ከንቱ ዘመን በዋዛ ፈዛዛ የሚባክን ስአት የለንም:: የጅምላ ጥላቻን የመሰለ እና ሐይማኖትን ተኮር ያደረገ ትንኮሳ ከፍተኛ ብሔራዊ አደጋ ነው ::
  
  የዘር እና የብሔር ችግር እንዲፈጠር ማድረግ በሰከንዶች ውስጥ ሞትን አዝለው የሚመጡ አደጋዎች እንደሚከሰቱ ማወቅ ያስፈልጋል ::ዛሬ በሱማሌ ክልል ይምናየው እልቂት የዚህ ሰንካላ ምክኒያት ውጤት ነው :: የህዝብን ህይወት ሊያደፈርሱ የሚችሉ የጥላቻን መርዝ መንዛት እና ሰላማዊ ሰዎችን መግደል ፣ ማፈናቀል ከዚህ በላይ ብሔራዊ አደጋ ሊኖር አይችልም :: 
  
  በግልፅ መናገር ካስፈለገ ሐገራችን በታላቅ ችግርና ፖለቲካዊ ነውጥ ውስጥ ለማስገባት ከአብይ እና ከኢትዮጵያ ህዝብ የመደመር አላማ በተፃራሪ የቆሙ ሾተላዮች ፣ ሐይላቸውን እና ገንዘባቸውን አስተባብረው ዘመቻ ከፍተውብናል :: በእርግጥ የአብይም ሆነ የለማ መገርሳ አስተዳደር የራሳቸውን በጎነት ጨምረው ቢያንስ ፈጣሪንና ህሌናን ዳኛ ያደረገ የአንዲት ኢትዮጵያን እውን መሆን የመደመር ስሌት እየሰሩ ነው :: ይህን ሞራልን መሰረት ያደረገ ስርአት ለማምጣት የአብይ እና የለማ ብቻ ሀላፊነት መሆን የለበትም :: ዜጎች ሁሉ በበጎ አስተሳሰብ በጋራ አብረናቸው መነሳት አለብን :: 
  
   ሞታቸው ሞታችን ድላቸው ድላችን መሆን አለበት :: ዛሬ ሐገራችን በቀን ጅቦችና በሾተላዮች ስትታመስ እያየን እየሰማን ተመልካች ብቻ የምንሆን ከሆነ በእርግጥም ሐላፊነት የማይሰማን ዜጎች ነን ማለት ነው ::  ዝም ብለን በደመነፍስ መጏዝ የለብንም :: ታላቅ ሐገር ታላቅ ሕዝብ እንዲኖረን የምንመኝ ከሆነ ችግራችንን ሁሉ መንግስት ይቅርፈዋል ብለን መጠብቅ የዋህነት ነው :: ይህ እንደባሕል አርገን የወሰድነው በሰው መስዋዕትነት መኖር ማብቃት አለበት :: ህብረተሰቡ እራሱን መጠበቅ መለማመድ እና መሞከር አለበት ::
  
  ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ደጋግመው እንደ ገለፁት ከሆነ የሐገራችን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካንም ሐላፊነት ተሸክመናል ::  በሐገራችን በሱማሌ ክልል የተከሰተው አይነት ያለ ችግር ለዘለቂታው ለመፍታት የሚደረገው ጥረት በግብታዊነት ሳይሆን ጥናትና ምርምር ማካሂድ አለብን :: ኢትዮጵያዊነት እንደህዝብ እንደሐገር እንደ መንግስት መታወቅና መከበርን ከሁሉም በላይ የነፃነትን እሴቶቻችን መሰረት ያደረገ እንደመሆኑ ከነፃ ህዝብነት የሚፈልቀውን ልበሙሉነትና የመንፈስ እርካታ ሁሉ ያጎናፀፋል :: ካለበለዚያ  ዝም ብሎ የማንም ውርጋጥ ጭቃ እያድቦለቦለ ጠፍጥፎ የካርታ ሐውልት የሚያቆምበት ስርአት ለመመስረት እና ህዝብን ለመከፋፈል አይደለም የምንደክመው :: 
  
   ሐገራችን ኢትዮጵያ የጋራ ታሪክ ያለው ሰንደቅ አላማ አላት :: የተባበሩት መንግስታት እውቅና ያለው አረንጏዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ሰንደቅ አላማ ::  በሐገራችን ሆነ በመላው አለም በኩራት የምናውለበልበው ፀረ ኮሎኒያሎኒያሊዝምን አባቶቻችን የአንበረከኩበት  ብሔራዊ ሰንደቅ አላማችን ነው :: የእኛነታችን መገለጫ :: በዘፈቀደ ማንም ሰው ልብስ ሰፊ ቤት እየሔደ ጣቃ እያስቀደደ ሕዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚነሳሳ ምልክት አንስቶ መፎከር የለበትም ::
  
   የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ያስገኘውን ታላቅ ቅርስ ሐላፊነት በጎደላቸው ውርጋጦች ሲደፈር ማየትም ተገቢ አይደለምና ሊታሰብበት ይገባል እንላለን :: ለምን የጋራ ጠላቶቻችንን ለማስዎገድ በጋራ መቆም የሰከነ ዘመናዊ መንግስት ለማቋቋም በግስጋሴ ላይ ነው ያለነው :: በተለይ የሐገርን ታሪክ ጠንቅቆ አለማወቅ አላማ ቢስነትና የመቻቻል ባህልን አለመለማመድ ታላቅ የመደመር እንቅፋት ሲሆን ለዲሞክራሲ ስርአት ዃለቀር ውርሶች ናቸው :: እናም በአስተሳሰብ ደርጃ ያሮጌው ባህላችን ነፀብራቅ አሚካላ በመሆናቸው በጋራ ነቅለን መጣል አለብን  :: በዚህ ጉዳይ የነፍስ ጨለማን የሚያበሩት ለማ መገርሳ በህይወት ያሉ የአንድነት ሐውልት ትልቅ ምሳሌ ናቸው :: አሁንም ለማ መገርሳ መጣ እያገሰ ማለታችን ይቀጥላል ::
  
  ለዛሬው በዚሁ አበቃሁ በሌላ ዝግጅት እስክንገናኝ ቸር ይግጠመን
  
  አለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)
  
  « Back to archive
 • Leave your comment

 • Name:
   
  Email:
  Comment   
  captcha
  Enter the code shown above: