• News

 • የማይጨርሱትን አይጀምሩትም! 25 March 2019 | View comments

 • የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር በይፋ ሥራ ከጀመረ አንድ ዓመት ሊሆነው ቀናት ብቻ ይቀሩታል፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ የተከናወኑ ሥራዎችና ያጋጠሙ ችግሮች በግልጽ ይታወቃሉ፡፡ ኢትዮጵያ ለዘመናት ሲንከባለሉ ከመጡ ችግሮች ተላቃ ወደ ታላቅ አገርነት ሊያሸጋግሯት የሚችሉ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች የታዩትን ያህል፣ ዓይታው ወደማታውቀው አደገኛ ቁልቁለት የሚያንደረድሯት ክስተቶችም አጋጥመዋታል፡፡ በዚህ ወቅት እነዚህ ሁለት የተለያዩ ወይም ተቃራኒ ሁነቶች ማጋጠማቸው አይደንቅም፡፡ ነገር ግን ተስፋ ሰጪ ጅምሮችን ተስፋ የሚያስቆርጡ ክስተቶች ሲበዙ ግን ለምን መባል አለበት፡፡ አንዱ ባለቤት ሌላው ባዕድ የሆነባት አገር ሳትሆን፣ ሁሉንም ወገን በነፃነትና በእኩልነት ማስተናገድ የምትችል የጋራ የሆነች አገር ነው የምትፈለገው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር ተነቃንቆ ለአዲሱ አስተዳደር ድጋፍ የሰጠው፣ በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ዴሞክራሲያዊት አገር ለመገንባት በነበረው ፅኑ ፍላጎት እንደነበር ከቶውንም ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ይህንን የጋራ ግንዛቤ የሚሽሩና የአንድ ወገን የበላይነት ለመጫን የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ያለ ምንም ይሉኝታ የሚያሳዩት አዝማሚያ አንድ ቦታ ላይ መቋጫ ማግኘት አለበት፡፡ ሕዝቡ ለውጡን ደግፎ የተነሳው የዓመታት በነፃነት የመኖር ህልሙን ለማሳካት እንጂ፣ ተረኛ ጉልበተኛ ጫንቃው ላይ ለማስፈር አይደለም፡፡ ይህ ቢሆን ኖሮ ተጀምሮ የማያልቅ ነገር ውስጥ አይገባም ነበር፡፡

  በየትኛውም ሥፍራ አገር የሚመሩ ግለሰቦች ተቀዳሚ ዓላማ አስተዳደራቸውን በሚገባ መቆጣጠር ነው፡፡ እንደኛ ባሉ አገሮች ደግሞ አንድ መሪ የገዛ ፓርቲውንና አስተዳደሩን መቆጣጠር ይጠበቅበታል፡፡ በፓርቲውና በአስተዳደሩ ላይ ሊኖረው የሚገባውን ቁጥጥር ካጣ፣ አገር የሕገወጦችና የሥርዓተ አልበኞች መጫወቻ ትሆናለች፡፡ መንግሥት የሕዝብን ደኅንነትና  ሰላም፣ እንዲሁም የአገርን ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም የማስጠበቅ ኃላፊነትና ግዴታ አለበት፡፡ መንግሥትን በበላይነት የሚመራው ግለሰብ ደግሞ ይህ ኃላፊነትና ግዴታ ለአፍታም እንዳይጓደል ከማንም በላይ ተጠያቂነት አለበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በዚህ መንገድ የመወጣት ግዴታ ሲኖርባቸው፣ ካቢኔያቸው በተለያዩ የሥራ መስኮች ዕገዛ የማድረግ ተልዕኮውን መወጣት አለበት፡፡ ፓርላማው ደግሞ የአስፈጻሚውን መንግሥት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የመቆጣጠር ኃላፊነት የእሱ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የፓርቲ ወይም የአስተዳደር አመራሮች ሲያፈነግጡ፣ የጎንዮሽ ግንኙነት እየፈጠሩ ከሌሎች አካላት ጋር ሴራ ሲጎነጉኑና ሕገወጥነትን ሲያስፋፉ ጦሱ የሚተርፈው ለአገርና ለሕዝብ ነው፡፡ ይህ በአንክሮ መታየት ይኖርበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት ለወጣቶች፣ ‹‹አዲሱ ትውልድ በአሮጌ አስተሳሰብ አይመራም›› እንዳሉት፣ ለዘመኑ የማይመጥን ተረት እያግበሰበሱ አገርና ሕዝብ የሚያምሱትን ማስቆም አለባቸው፡፡ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ሽግግሩን መምራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሕዝብ በዚህ ተማምኖ ነው ከጎናቸው የተሠለፈው፡፡

  ያለፉት 12 ወራት ጉዞ ሲገመገም እንደተለመደው መልካም የሚባሉ ጉዳዮች ውስጥ ተቀርቅሮ አሳሳቢ ነገሮችን መዘንጋት በፍፁም አይገባም፡፡ በእርግጥም በርካታ ተስፋ የሚሰጡ ተግባራት ተጀምረዋል፡፡ የዜጎችን ነፃነት የሚጋፉ ሕጎች ተሻሽለው እንዲወጡ አመርቂ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ የሚያሸጋግሩ በርካታ ጅምሮች አሉ፡፡ ከጎረቤት አገሮች ጋር የነበረው ግንኙነት በተሻለ ደረጃ እንዲጠናከርና ትስስር እንዲፈጠር እየተሠራ ነው፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በአጥጋቢ ሁኔታ ሥራ ላይ እየዋለ ነው፡፡ በየቦታው ውይይቶች በነፃነት እየተካሄዱ ነው፡፡ ምርጫን ተቀባይነት ባለው መሥፈርት ለማካሄድ የሚያስችሉ በጎ ጅምሮች እየታዩ ነው፡፡ ሌሎችም ተስፋ የሚሰጡ ክንውኖች ይታያሉ፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ በሽግግር ጊዜ የሚያጋጥም ቢሆንም በርካታ እንቅፋቶች በየቦታው ይስተዋላሉ፡፡ መረር የሚለው ግን ፖለቲከኞች በሚጭሩት እሳት በሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ሞት፣ መፈናቀልና ስደት ነው፡፡ በተለይ ትልቁን አገራዊ ምሥል ማየት በማይፈልጉ ኃይሎች አማካይነት በሕዝብ ላይ እደረሰ ያለው ሰቆቃ ለአገር ህልውናም እያስፈራ ነው፡፡ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በማንኳሰስ ክልልተኛና ጎጠኛ የሆኑ ከፋፋይ ቅስቀሳዎችን በይፋ የሚያውጁ ኃይሎችን፣ በሕግ የበላይነት አደብ ማስገዛት አለመቻል አደጋው የከፋ ነው፡፡ የተጀመረውን ለውጥ አስቀልብሶ ሌላ ጣጣ ውስጥ ይከታል፡፡ ምነው ባልጀመርኩትም ማለት ይከተላል፡፡

  የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሰላም የሚሰጠው ዋጋ ትልቅ ነው፡፡ ይህ ረቂቅ የሆነ ሕዝብ ክብር ይገባዋል፡፡ በሰላም፣ በነፃነትና በእኩልነት መኖር አለበት፡፡ ይህች አገር ታሪኳ የጦርነት ነው፡፡ በመሳፍንቶች መካከል ከሚደረጉ ግጭቶች እስከ አገርን ከወራሪ የመከላከል ጦርነቶች ድረስ ከፍተኛ መስዋዕትነት ሲከፈል ተኑሯል፡፡ በዚህም ምክንያት በተፈጥሮ ሀብት የታደለችው ኢትዮጵያ ከድሆች ተርታ ግንባር ቀደም መሪ ሆናለች፡፡ ድርቅ፣ ረሃብ፣ ኋላቀርነትና ማይምነት መታወቂያዋ ነበሩ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከዚህ ዓይነቱ አረንቋ ውስጥ ለመውጣት ጥረት ተጀምሮ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ሰላም በማስፈን በኅብረት መነሳት ከተቻለ ደግሞ ይህንን መሳይ ሕዝብ ይዞ ተዓምር መሥራት ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ዕውቀታቸውን፣ ልምዳቸውንና ሀብታቸውን ለማበርከት ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ፍላጎታቸውን አሳይተዋል፡፡ በአገር ውስጥ የሚገኙ አገር ወዳዶችና ምሁራንም በከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት ተነሳስተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በገንዘቡም ሆነ በጉልበቱ አለሁ ብሏል፡፡ ይህንን ወርቃማ ዕድል በመጠቀም በአግባቡ አመራር መስጠት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት መንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ የተጀመረው ለውጥ በአግባቡ መከናወን የሚችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ በጎን እየመጡ የሕዝቡን የዘመናት ህልም እያደናቀፉ ያሉ ኃይሎችን በሕግ ማስታገስ ይገባል፡፡ ካሁን በኋላ የጉልበት መንገድ እንደማያወጣ ዕቅጩን ተናግሮ ወደ ሥራ መግባት የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ካልተቻለ ደግሞ ቁርጡን መናገር ነው፡፡

  ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ለልዩነቶች ዕውቅና ሰጥቶ በአንድነት ለጋራ ዓላማ መሠለፍ፣ በሐሳብ የበላይነት ማመን፣ በአገራዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ መወያየትና መደራደር መቻል ነው፡፡ ጥሩ የሠራን ማመስገን፣ ያጠፋን መተቸት ወይም መገሰፅም መለመድ አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ ጊዜው ተመችቶኛል በማለት እብሪትና ጥጋብ ማስተጋባት ተቀባይነት የለውም፡፡ በውይይት መፈታት የሚችሉ ጉዳዮችን ለገላጋይ የሚያስቸግር ጠብ ውስጥ መክተት፣ እያንዳንዱን ነገር በብሔር መነጽር ብቻ ማየት፣ ፍትሕና እኩልነትን የሚያዛቡ ድርጊቶችን መፈጸም፣ ሕግ ባለበት አገር ውስጥ ሕገወጥ መሆን፣ ሕዝብ ተስፋ ያደረገበትን ለውጥ ላልተገባ ዓላማ ማዋልና የመሳሰሉት ለአገር አይጠቅሙም፡፡ አገርን የምታህል ትልቅ ነገር ይዞ የበለጠ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ሲገባ፣ መንደር ውስጥ ተቀርቅሮ ማላዘን ያስገምታል እንጂ ፋይዳ የለውም፡፡ ሕዝብን ነጋ ጠባ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በእምነትና በመሳሰሉት በመከፋፈል ማጋጨትና ማተራመስ ኋላቀርነት ነው፡፡ አሜሪካና አውሮፓ አቅፈው በክብር እያኖሯቸው አገር ቤት ያለውን ወገናቸውን እርስ በርስ ማባላት ነውረኝነት ነው፡፡ ይህ ዘመን በአንድነት በመቆም ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ፣ ከድህነትና ከተዋራጅነት የማውጣት ኃላፊነት በዚህ ትውልድ ላይ ጥሏል፡፡ ታሪክም ይኼንን ይመዘግባል፡፡ በዚህ መንፈስ አንድ ዓላማ ጨብጦ መንቀሳቀስ ካልተቻለ፣ መጪው ትውልድና ታሪክ ይፋረዳሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ህልሙ ተሳክቶ በነፃነትና በእኩልነት መኖር ይፈልጋል፡፡ ይኼንን ዓላማ ለማሳካት የተጀመረው ለውጥ በመላ ኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል እንጂ መቆም የለበትም፡፡ ለዚህም ነው የማይጨርሱትን አይጀምሩትም የሚባለው

   

  Source: www.ethiopianreporter.com

  « Back to archive
 • Leave your comment

 • Name:
   
  Email:
  Comment   
  captcha
  Enter the code shown above: