• News

 • መጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ;-"አይቼው የማላቀው የድንጋይ መጽሐፍ" 01 February 2020 | View comments

 • [አይቼው የማላቀው የድንጋይ መጽሐፍ]
  በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
   ባለፈው እንዳስነበብኳችሁ በሰሜን አሜሪካ ኮንግረስ ቤተ መጻሕፍት በቶማስ ጄፈርሰን ሕንጻ ውስጥ ወደ 250 የሚጠጉ የኢትዮጵያ ጥንታውያን የብራና መጻሕፍትን ተፈቅዶልኝ ካየሁ በኋላ የቀረጽኳቸውን መላልሼ በማየት በመደነቅ ጊዜዬን ማሳለፍ ጀመርኩ።

   ከልጅነት ጀምሮ በብራና መጻሕፍት ውስጥ ማደጌ ይመስለኛል ብራና መጻሕፍት ያሉበትን ክፍል በማሽተት ጭምር ሳለየው አልቀርም። እነዚህን የቀደምት ኢትዮጵያውያኑን መጻሕፍት ስለምወዳቸው ይመስለኛል መዋደድ የጋራ ነውና በምሄድበት ሀገራት ሁሉ በፍቅር ይጠብቁኛል።

   ኮንግረስ ላይብረሪ ባየሁት 250 መጻሕፍት ስደነቅ 800 የብራና መጻሕፍት ያሉበት ታላቅ ዪኒቨርሲቲ እንዳለ ይልቁኑ የድንጋይ የግእዝ መጽሐፍ እንዳለ መምህር ነጸረ አብ ቁጭ ብለን ስናወጋ በጆሮዬ ሹክ አለኝ። በመገረም በመደመም ውስጥ ሆኜ ለጥቂት ደቂቃዎች ጸጥ ካልኩ በኋላ ቦታውን ስጠይቀው በካቶሊክ ዪኒቨርሲቲ ኦፍ አሜሪካ እንደሆነ በቦታው 15 ዓመታት የሠራው መምህር ነጸረ ነገረኝ።

   ካቶሊክ ዪኒቨርሲቲ ኦፍ አሜሪካ የተመሠረተው በ1887 ዓ.ም ሲሆን ታላቅ ጥናትና የምርምር ሥራ የሚደረግበት ዪኒቨርሲቲ ነው። በስሩ ባሉት 12 ትምህርት ቤቶች ውስጥ በፒ ኤች ዲ ዶክትሬት (Doctor of Philosophy) 66 በማስተርስ ዲግሪ 103፤ በቅድመ ምረቃ 72 ፕሮግራሞችን በመስጠት ተመራማሪዎችን ለፕላኔቷ ያቀርባል። 
  የእኛው ቋንቋ ግእዝም እስከ ፒ ኤች ዲ የዶክትሬት ዲግሪ ከሚሰጥባቸው ታላላቅ ዓለም ዐቀፍ ዪኒቨርሲቲ ውስጥ አንደኛው ይህ ነው።

   በቅድመ ምረቃ 3332 በድኅረ ምረቃ 2624 በአጠቃላይ ወደ 5956 የዛሬ ተማሪዎች የነገ ተመራማሪዎች አሉት። ከUS Capitol በ3 ማይል ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ የምርምር ዪኒቨርሲቲ ሰፊና በ176 ሔክታር ላይ ያረፈ ለዐይን ማራኪ ነው። በዪኒቨርሲቲው ያለው የጆን ኬ ሙሌን መታሰቢያ ቤተ መጻሕፍት ከ1.3 ሚሊየን በላይ መጻሕፍት፤ በ10ሺዎች የሚጠጉ ኤሌክትሮኒክ ጆርናሎች ይገኙበታል።

   ይህን ታላቅ የምርምር ተቋምን ማየት እንድችል ይልቁኑ የምወዳቸው የኢትዮጵያን ጥንታውያት መጻሕፍት እንድመለከት ስለተፈቀደልኝ ኅዳር 28 እሑድ ወደ ዪኒቨርሲቲው ከመምህር ነጸረ ከካሜራ ማኖቼ ከኤርሚና ከደመኢየሱስ ጋር ሄድን።

   ወደ ውስጥ ዘልቀን ከገባን በኋላ የኢትዮጵያ ጥንታውያት የብራና ስብስብ ወዳለበት የምድር ቤቱ ክፍል ወረድን። ወደ ክፍሉ ስንቃረብ ዕውቀትን ያመቁ የብራና መጻሕፍት ሽታ ተሰማኝ፤ ገብቼ እስከምመለከታቸው ድረስ አላስቻለኝም፤ የክፍሉን መጥሪያ ስንነካው ከውስጥ የሲሪያክ፣ የአርመን፣ የጆርጂያ ቋንቋዎች ፕሮፌሰር የሆነችው የክፍሉ ሐላፊ ዶክተር ሞኒካ ብላንቻርድ በሩን ከፍታ በፈገግታ ተቀበለችን። 

   ረጅሙን የሕይወት ዘመኗን በጥናት በምርምር እንዳሳለፈች ያስታውቃል፤ ወዲያውኑ ጊዜ አልወሰደችም በብራና መጻሕፍት ወደተሞላው በጥንቃቄ በንጽሕና በተቀመጡበት ክፍል ውስጥ አስገብታን ዕርፍ።

   የፈለጋችሁትን አውጥታችሁ እዩ ወደ 400 የሚጠጉ ታላላቅ የብራና መጻሕፍትና 400 ጥቅሎች አሉላችሁ አለችን እኔም እየመረጥኩ መመልከት ጀመርኩ። ብራናዎችን ሳነባቸው የኖሩኳቸው ወዳጆቼ በመሆናቸው ከእነርሱ ጋር ለተወሰነ ሰዓት የተመስጦ ቆይታ አድርጌ ወደ 400 ጥቅሎች አመራሁ ግን ስንቱ ተነቦ ያልቃል? ብቻ የምፈልጋቸውን ከተመለከትኩ በኋላ በድንጋይ ላይ የተቀረጹ የጥንታውያን ቋንቋዎች ጽሑፎችን አየሁ።

   የድንጋይ ላይ ጽሑፎችን ማን ይተረጉማቸዋል? እያልኩ ስቆዝም ዶክተር ሞኒካ ሳይገባት አልቀረም ፊደላት የተቀረጸበት በእጇ ቡናማ ወረቀት ይዛ ጠጋ ብላ አዲሱን ግኝት አስተዋወቀችኝ፤ ይኸውም በቀላሉ የድንጋይ ላይ ጽሑፍን ወደ ወረቀት ላይ ለውጦ በጉልሕ ያስነብባል፤ ለትርጓሜው ችግር የለም ቀንና ሌሊት ያለዕረፍት የሚመራመሩ የቋንቋዎች ሊቃውንት ይተረጉሙታል።

   ይህን በተመስጦ ስመለከት በኅሊናዬ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ሳይንሳዊ ዕውቀቶችን ጠራርጎ አሽቀንጥሮ ጥሎ ዓለም አሁን የደረሰበት ዕውቀት ሳይደርስበት የመደባደቢያ አውድማ የሆኑትን የሀገራችን የትምህርት ተቋማት ሳስብ ሐዘን ተሰማኝ።

   ነገር ግን ነገ ኢትዮጵያን የሚረከቧት ዛሬ ትውልዱ የዘነጋቸው ሕፃናት ትውልዱ በዝንጋኤ የጣለውን የኢትዮጵያን አልማዛዊ ዕውቀት በክብር አንሥተው ዓለም ከደረሰበት የሳይንስ ምርምር ጋር አስተባብረው ኢትዮጵያን በከፍታ ሰገነቷ ላይ እንደሚያስቀምጧት ስለማምን ሐዘኑ ከልቤ ብን ብሎ ወጣ።

   በመጨረሻም ዶክተር ሞኒካ ላየው የምፈልገውን የድንጋይ ላይ ተከፋች የግእዝ ጽሑፍን ያለበትን ይዛ መጣች፤ በሕይወቴ እንደዚህ ዓይነት አይቼ ስለማላውቅ በአድናቆት ተመላሁ።በድንጋይ ላይ ጽሑፍንና ሥዕልን መቅረጽ የሚችሉ ጥበቦች ኢትዮጵያውያን እንደነበሩ አይቼ የበለጠ አከበርኳቸው። ጣቶቼም እነዚያን ጽሑፎች ዳሰሱ።

   ምስለ ፍቁር ወልዳና ሥዕለ ሥሉስ ቅዱስ ከታተመበት ከዚ የድንጋይ ጽሑፍን ስገልጥ ረዘም ያለ የዘንባባ ሥዕል ዳርና ዳር ያለው የአንዲት የንግሥት ሴት ከፊል ገጽ ና የአንድ ወንድ ተቀርጾ ይታያል።

   የሴቲቱ አቀራረጽና ሹሩባን ስመለከተው በጥንት የኢትዮጵያ ኑብያና ግብጽ ሥልጣኔ የምናያቸው ንግሥታትን ይመስላልና፤ የኢትዮጵያ ልዕልት አንድሮሜዳ ትሆን? ብዬ አሰብ አረኩና ረጃጅሞች የዛፍ ቅርጾች ግን ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ በመመርመር የጥንታውያን የኢትዮጵያን ከፍተኛ ሥልጣኔ ታሪክ የሚያውቁት ሐኪም አበበች ሽፈራውን እጠይቃቸዋለሁ በማለት ገጥሜ በነበረበት የክብር ስፍራ አስቀመጥኩት።

   ለ15 ዓመታት በዚህ ቤተ መጻሕፍት የሠሩት መምህር ነጸረ አብ በመጨረሻ ሲነግሩኝ ያሳዘነኝ ነገር እነዚህን መጻሕፍት ለመመርመር እጅግ ብዙዎች ዓለም ዐቀፍ ተመራማሪዎች ወደ ቤተ መጻሕፍቱ ዘወትር ሲመጡ በ16 ዓመት ውስጥ መጥቶ ያየው አንድ ኢትዮጵያዊ ብቻ ነው ሲለኝ መስማቴ ነው፤ አባቶች ሁሉን ሠርተው ፍሪጅ ውስጥ አስቀምጠው ቢሄዱም ከስንፍና ብዛት አውጥቶ አሙቆ መብላት ያቃተን ያህል እየተሰማኝ በቀዝቃዛው የማታው አየር ሰፊውን የዩኒቨርስቲውን ቅጽር ለቅቄ ስወጣ ልቤ ግን በውስጥ ካሉት ከ800 መጻሕፍት ጋር ነበር።

  [ኅዳር 28/ 2012 ዓ.ም በሰሜን አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የካቶሊክ ዪኒቨርሲቲ ኦፍ አሜሪካ ቆይታዬ] 
  https://t.me/joinchat/AAAAAFTyR7tztt08pN9U-w
   መጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ

  « Back to archive
 • Leave your comment

 • Name:
   
  Email:
  Comment   
  captcha
  Enter the code shown above: