• News

 • ክቡር ሚኒስትሩ ከወዳጃቸው ጋር 28 May 2015 | View comments

 • [ክቡር ሚኒስትሩ ከወዳጃቸው ጋር ቢሯቸው ተገናኙ]

  -ኳስ ይወዳሉ ክቡር ሚኒስትር?

  -ኳስ እኮ ሁለተኛ ሃይማኖቴ ነው፡፡

  -የመጀመሪያ ሃይማኖትዎ ምንድነው?

  -አብዮታዊ ዲሞክራሲ፡፡

  -እሱ ሃይማኖት መሆኑን አላውቅም ነበር፡፡

  -ለእኔ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከሃይማኖትም በላይ ነው፡፡

  -ከሃይማኖት በላይ ደግሞ ምን ሊሆን ነው?

  -ለእኔ ሕይወቴ ነው፣ ሁሉ ነገሬ ነው፡፡

  -ክቡር ሚኒስትር ሕይወትዎ ይቀያየራል ማለት ነው?

  -ምን ማለትህ ነው?

  -ያኔ ጫካ እያላችሁ እኮ ሶሻሊዝም ሕይወቴ ነው ይሉኝ ነበር፡፡

  -የማይቀየር ነገር ምን አለ ብለህ ነው?

  -ለነገሩ እውነትዎትን ነው፤ ይኸው ኢትዮጵያ ራስዋ ተቀይራለች አይደል?

  -እሱን እኮ ነው የምልህ? ሁሌም መገላበጥ ጥሩ ነው፡፡

  -ያልተገለበጠ ያራል አይደል ተረቱ?

  -ካልተገላበጥክ እኮ ትገለበጣለህ፡፡

  -ጊዜው የመገለባበጥ ነው እያሉኝ ነው?

  -ጊዜውማ የኢሕአዴግ ነው፡፡

  -የሻምፒየንስ ሊግን ይከታተላሉ?

  -ስነግርህ ከፖለቲካ ቀጥሎ እግር ኳስ ነው የምወደው፡፡

  -ለነገሩ ኳስና ፖለቲካ እኮ ተመሳሳይ ናቸው፡፡

  -እንዴት ሆኖ?

  -በመጀመሪያ ሁለቱም ጨዋታ ናቸው፡፡

  -አልገባኝም?

  -አንደኛው የኳስ ጨዋታ ነው፤ ሌላኛው የፖለቲካ ጨዋታ ነው፡፡

  -እሺ፡፡

  -ሁለቱም ጨዋታ ላይ ደግሞ ተፎካካሪ አካላት አሉ፡፡

  -እሱስ ልክ ነው፡፡

  -በሁለቱም ጨዋታ ላይ ዳኛ አለ፡፡

  -እርግጥ ነው፡፡

  -ታዛቢም አለ፡፡

  -ሌላስ?

  -ሁለቱንም ጨዋታዎች ሕዝብ ሁሌም በጉጉት ይጠብቃቸዋል፡፡

  -ልክ ብለሃል፡፡

  -ለማንኛውም የማን ደጋፊ ነዎት?

  -እኔ ደጋፊ ሳልሆን ተወዳዳሪ ነኝ፡፡

  -የሻምፒየንስ ሊጉ ጨዋታ ላይ ማለቴ ነው፡፡

  -ለባርሳ ነኛ፡፡

  -ለማን አሉኝ?

  -ለገዢው ቡድን፡፡

  -ማነው ገዢው?

  -አውራው ነዋ፡፡

  -እኮ ማነው አውራው?

  -ባርሳ አልኩህ፡፡

  -እኔ ግን ተፎካካሪው ቢያሸንፍ ደስ ይለኛል፡፡

  -ተቃዋሚዎች?

  -የለም ጁቬንትስ ማለቴ ነው፡፡

  -አውራው እንደሚያሸንፍማ የተረጋገጠ ነው፡፡

  -እንዴት ክቡር ሚኒስትር?

  -በርካታ ቡድኖችን አሸንፎ ነው እዚህ የደረሰው፡፡

  -ተፎካካሪውም ቢሆን እኮ ቀላል አይደለም፡፡

  -ምን እያልከኝ ነው?

  -ተፎካካሪው አካል በርካታ መንገዶችን አልፎ ነው እዚህ የደረሰው፡፡ 

  -እና ተቃዋሚዎች ገዢውን ፓርቲ ያሸንፋሉ እያልክ ነው?

  -የለም እኔ ስለጁቬንትስ ነው እያወራሁ ያለሁት፡፡

  -እህህህ… እሱንማ ነገርኩህ ዋንጫው የባርሳ ነው፡፡

  -የማን ነው አሉኝ?

  -የገዢው፡፡

  -ለምን ክቡር ሚኒስትር?

  -ዳኞች ራሱ ለእርሱ ነው የሚያግዙት፡፡

  -ለምን ያግዛሉ?

  -የዛሬ ስድስት ዓመት ቼልሲ ከባርሴሎና ጋር ለዋንጫ ለማለፍ የተጫወቱት ጨዋታ ትዝ ይልሃል?

  -እስቲ ያስታውሱኝ?

  -በዚያ ጨዋታ ቼልሲ ንፁህ አራት የፍጹም ቅጣት ምት አልተሰጠውም፡፡

  -አዎን ትዝ አለኝ፡፡

  -ለምን እንደዚያ እንደሆነ ታውቃለህ?

  -አላውቅም፡፡

  -ከቼልሲ ይልቅ ባርሴሎና ቢያልፍ ትልቅ ትርፍ ከቴሌቪዥን ማስታወቂያ ስለሚገኝ ነው፡፡

  -ስለዚህ ዳኛዎችም ለባርሳ ይደግፋሉ እያሉኝ ነው?

  -እንዴታ ገዢውን ማን የማይደግፍ አለ?

  -ሁሌም ግን እንደዚህ አይመስለኝም፡፡

  -እስቲ አንድ ምሳሌ ስጠኝ?

  -የዛሬ አሥር ዓመቱ የዋንጫ ጨዋታ ትዝ ይልዎታል?

  -መቼ የተደረገው?

  -በ97 አልኩዎት፡፡

  -የ97 ምርጫን ነው?

  -የለም የለም፣ በዚያ ዓመት የተካሄደው የሻምፒየንስ ሊግ የዋንጫ ጨዋታ፡፡

  -እስቲ አስታውሰኝ፡፡

  -ለዋንጫ የደረሱት ሊቨርፑልና ኤሲ ሚላን ነበሩ፡፡

  -እሺ፡፡

  -ለኤሲ ሚላን ከፍተኛ ግምት ሲሰጠው ተፎካካሪው ግን አነስተኛ ግምት ነበር የተሰጠው፡፡

  -ከዚያስ?

  -ከዚያማ ኤሲ ሚላን በጨዋታው ሦስት ለዜሮ ሲመራ ቆይቶ ኋላ ላይ ውጤቱ ተቀየረ፡፡

  -ውጤቱ ምን ሆነ?

  -ያልተጠበቀው ተፎካካሪ አሸነፈ፡፡

  -በ97 ምርጫ ተፎካካሪዎቻችን መቼ አሸነፉ?

  -ኧረ እኔ ኳሱን ነው ያልኩዎት፡፡

  -እ…

  -ለነገሩ በኢትዮጵያ ምርጫም ቢሆን ያልተጠበቀ ነገር ነበር የተከሰተው፡፡

  -እንዴት?

  -ያው ተቃዋሚዎች በርካታ የፓርላማ መቀመጫዎችን አሸንፈው ነበራ፡፡

  -ቢሆንም ግን አሸናፊው ፓርቲ የእኛው ገዢ ፓርቲ ነበር፡፡

  -ዋናው ነጥቤ እሱ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡

  -ምንድነው ታዲያ?

  -ጨዋታው ፌርና ክሬደብል ሊሆን ይገባዋል፡፡

  -ለምን?

  -ፌርና ክሬደብል ካልሆነ ተወዳጅም አይሆንም፡፡

  -የፖለቲካ ጨዋታውን ነው የምትለኝ?

  -የፖለቲካውም ሆነ የኳሱ ጨዋታ፡፡

  -ስለዚህ ዳኛዎቹ ነፃና ገለልተኛ መሆን አለባቸው እያልከኝ ነው?

  -በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፤ ምክንያቱም ዳኛዎቹን የሚዳኝ ሌላ ዳኛ እኮ አለ፡፡

  -ማነው እሱ?

  -ሕዝቡ፡፡

  -የትኛው ሕዝብ?

  -ተመልካቹ ነዋ፡፡

  -አሃ… ለካ ዳኛዎቹ ሜዳ ላይ ቢዳኙም፣ ሕዝቡ በየቤቱ ዳኛ ነው፡፡ 

  -አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡ 

  -ስለዚህ የፖለቲካ ጨዋታው ዳኛም ነፃና ገለልተኛ ሊሆን ይገባል እያልከኝ ነው?

  -ዳኛው ነፃና ገለልተኛ ካልሆነማ፣ የጨዋታው ተዓማኒነት ይቀንሳል፡፡ 

  -ወይ ጣጣ፡፡

  -በዚያ ላይም ታዛቢም አለ፡፡

  -የምን ታዛቢ?

  -አራተኛ ዳኛው ነዋ፡፡

  -የእሱ ሥራ ደግሞ ምንድነው?

  -ጨዋታውን መታዘብ፡፡

  -ታዝቦ ሲያበቃ ምን ያደርጋል?

  -የእሱ ሪፖርት ለጨዋታው ተቀባይነት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

  -በደንብ ባይታዘብስ?

  -እሱንም ሕዝቡ ይታዘበዋል፡፡

  -ስለዚህ የፖለቲካ ጨዋታውም ታዛቢ ያስፈልገዋላ?

  -ለዚህኛውም ጨዋታ ተዓማኒነት የታዛቢው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

  -ወይ ጉድ፡፡

  -ስለዚህ ለጨዋታው ተዓማኒነትና ተቀባይነት ገዢውም፣ ተፎካካሪውም፣ ዳኛውም፣ ታዛቢውም በሚገባ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

  -ልክ ብለሃል፡፡

  [ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸው ጋ ደወሉ]  

  -አንተ ኳስና ፖለቲካ አንድ ዓይነት ናቸው እንዴ?

  -በርካታ የሚያመሳስሏቸው ነገሮች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡

  -ወይ ጉድ፡፡

  -ለምን ጠየቁኝ?

  -አይ ይኼንን እንደምታውቅ ለማወቅ ብዬ ነው፡፡

  -እና ለዋንጫው ጨዋታ ተዘጋጅተዋል?

  -አዎን ግን…

  -የምን ግን ነው ክቡር ሚኒስትር?

  -ለዚህ ጨዋታ እኮ ሕዝቡ ወሳኝ ነው፡፡

  -እንዴታ ክቡር ሚኒስትር? የጨዋታው ፈራጅ ሕዝቡ ነው፡፡

  -ታዲያ ለዚህ ሕዝብ ምን እናድርግለት?

  -እንግዲህ ያደረግነውን ነገር ሁሉ እስከዛሬ አስታውቀነዋል፡፡

  -አሁን ለሕዝቡ የምንመርቅለት ፕሮጀክት የለም?

  -ክቡር ሚኒስትር፣ ሁሉንም ፕሮጀክቶች አስመርቀናል፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ቦታ ላይ ደግመን ራሱ የመረቅናቸው ፕሮጀክቶች አሉ፡፡

  -አሁን ይኼ ሕዝብ ደግመን ደጋግመን ብናስመርቅለትስ ምን ይለዋል?

  -ከዚያም አልፈን ዕቅድ ላይ ለሌለ ፕሮጀክት ራሱ የመሠረት ድንጋይ ጥለናል፡፡

  -ኧረ ይኼ ሕዝብ ሲያንሰው ነው፡፡

  -እንዳይታዘበን ግን መጠንቀቅ አለብን፡፡

  -እንዳይታዘበን ነው እኮ የሚመረቅ ነገር ፈልግ የምልህ?

  -ምን ተሻለ ታዲያ?

  -ለምን ተማሪዎችን አናስመርቅም?

  -የትምህርት ዘመኑ ገና ነዋ፡፡

  -ወይ ጣጣ፡፡

  [ክቡር ሚኒስትሩ ቤታቸው ሲገቡ ሚስታቸውን አገኟቸው]  

  -ምነው ፊትህ ጠቋቆረ?

  -እንዴት አይጠቋቁር?

  -በቃ ምርጫ ሲደርስ ቀለምህ ራሱ ይቀያየራል?

  -እንዴት አይቀያየር?

  -እኮ ምን ሆነሃል?

  -ለካ ለዚህ ምርጫ ሕዝቡ ወሳኝ ነው?

  -ይኼን ሳታውቅ ነው እስከዛሬ ፖለቲከኛ የነበርከው?

  -አሁን ነው በእጅጉ የተገለጠልኝ፡፡

  -ከራስህ በፊት ሁሌም ሕዝቡን አስቀድም የምልህ ለዚህ ነው፡፡

  -አሁን እኮ እንዳይቀድመኝ ፈርቼ ነው፡፡

  -ሕዝቡማ ከቀደማችሁ ቆየ፡፡

  -ሳትቀደም ቅደም አሉ፡፡

  -ምን ልታደርግ ነው?

  -እየፈለግኩኝ ነው፡፡

  -ምን?

  [የክቡር ሚኒስትሩ ስልክ ጠራ]   

  -አቤት፡፡

  -አዎ ነኝ፡፡

  -ምን አልከኝ?

  -አለቀ?

  -አዎን እገኛለሁ፡፡

  -ታንኪው!

  [ክቡር ሚኒስትሩ ስልካቸውን ዘግተው ከሚስታቸው ጋር ማውራት ቀጠሉ]  

  -ምነው ደስ አለህ?

  -ተገኘ፡፡

  -ማነው የደወለልህ?

  -ያ የመኖሪያ ቤት የሚሠራው ዘመዴ ነው፡፡

  -ምን አለህ ታዲያ?

  -የመኖሪያ ቤቱን ጨረሰው፡፡

  -በጣም ደስ ይላል፡፡

  -ምን ደስ ይላል ብቻ፣ ገላገለኝ እንጂ፡፡

  -እንዴት?

  -እኔም ቤት አገኘኋ፡፡

  -የምን ቤት?

  -የሚመረቅ

  « Back to archive
 • Leave your comment

 • Name:
   
  Email:
  Comment   
  captcha
  Enter the code shown above: